እንደኔ አንዴ ሲቆጥቡት አንዴ ሲደብቁት በድንገት ዕድሜያቸዉ ወደ ሃምሳዎቹ የገባ ሰዎች አንድ የምንጋራዉ እምነት አለ- እሱም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች አንድ ነገር መጀመር እንጂ መጨረስ አያዉቁበትም የሚል እምነት ነዉ። በፍጹም ሊፈረድብን አይገባም። ከልጅነት ወደ አዋቂነት የደረስነዉ ጥንስስ ሲጠነሰስ እንጂ እንጄራዉን ሳናይ ነዉ። ፓርቲ ሲፈጠር እንጂ ዉጤቱን ሳናይ ነዉ። የፖለቲካ ህብረቶች ተፈጥረዉ ፈረሱ ሲባል ነዉ እንጂ እንዲህ አደረጉ ሲባል ሰምተንም አይተንም አናዉቅም። ባጠቃላይ የፖለቲካ ትግል ሲባል ነዉ እንጂ ድል ሲባል ሰምተን አናዉቅም። ድል የረጂም ግዜ ትግል ዉጤት እንደሆነ ይገባናል፥ ሆኖም ግን ዛሬ የሚረግጡን ሰዎች በረሃ ገብተዉ አዲስ አበባን እሲኪቆጣጠሩ ድረስ የወሰደባቸዉን ግዜ ሁላችንም የምናስታዉሰዉ ይመስለኛል። እኔ ይህንን ሁሉ ጉድ በአይኑ እያየ ያደገ ትዉልድ አካል ነኝ። ግን ይህንን ዕድሜ ልኬን ሲደጋገም ያየሁትን የአገሬን በሽታ መድሐኒት እፈልግለታለሁ እንጂ “ከመሳሳት እራሴን ላድናት” እኔን ምን አገባኝ የ”እነሱ” ጉዳይ ነው ብዬ እጆቼን አጣጥፌ አልቀመጥም። ጉዳዩ የኔ ነዉ . . .. ጉዳዩ የኛ ነዉ። “እነሱም” “እኛም” አንድ ላይ “እኛ” ነን። ሰዉ የመሆኔ ትልቁ ሚስጢር የሚነግረኝ በአካባቢዬ ካሉ ሰዎች ዉጭ መኖር የማልችል ማህበራዊ ፍጡር መሆኔን ነዉ። አንዳንዶቻችን መሳሳትን እንደ ጦር እንፈራለን፥ መሳሳትን ፈርተን እጃችንን አጣጥፈን ከምንቀመጥ እየተሳሳትንና ከስህተታችን እየተማርን የምንሰራዉ ስራ ነዉ አገራችንን ነጻ የሚያወጣት። ስለዚህ በእኔ እምነት ምንም ይሁን ምን ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሚጠበቅ ምንም ነገር የለም ብለን እጅና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጡ የበሽታ ምልክት ነዉ እንጂ የጤንነት አይመስለኝም።
እኔ ይህ የኔ ትዉልድ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት ያለበት የአደራ ትዉልድ ነዉ ብዬ የማምን ሰዉ ነኝ። ግን እንዴት ነዉ እኛ የኢትዮጵያ ልጆች በዘር፥በቋንቋና በሀይማኖት ሳንከፋፈል አንድ ላይ ቆመን ኢትዮጵያን አንድነቷ የተጠበቀ የፍትህ፥ የነጻነት፥ የእኩልነትና የዲሞክራሲ አገር የምናደርጋት? እንዴትና መቼ ነዉ ሁሉንም ያቀፈ ስብስብ ፈጥረንና በአንድ ጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠን የአገራችንን ችግሮች በዉይይት የምንፈታዉ? መቼ ነዉ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ማዶ ለማዶ ለያይቶ ካስጮኸንና ካጨቃጨቀን ማለቂያ የሌለዉ የባዶ ቃላት ጫጫታ ተላቅቀን ሞት አፋፍ ላይ የደረሰችዉን አገራችንን ከሞት የምንታደጋት? መቼ ነዉ ማንም ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊነት ሳይሰማዉ በኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚመለከታቸዉና ከሚያገባቸዉ ወገኖች ሁሉ ጋር ተቀምጠን ስለአገራችን ችግሮች የምንወያየዉና መፍትሄ የምንፈልገዉ? መቼ ነዉ በቋንቋ ብንለያይም፥ በሀይማኖት ብንለያይም፥ በሀሳብና በፖለቲካ አመለካከት ብንለያይም የጋራ የሆነዉ የአገራችን ጉዳይ አገናኝቶን በሰለጠነ ቋንቋ ተነጋግረን አዲስቷን ኢትዮጵያ አምጠን የምንወልዳት?
አብረነዉ ከቆምን፥ከተባበርነዉ፥ ከረዳነዉና ግዜና ሀሳብ ከሰጠነዉ እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ የሚችል አካል ጥንስስ ባለፈዉ ወር አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን ዲሲ ዉስጥ መጀመሩን ብዙዎቻችን ኢሳት በለቀቀዉ ሰበር ዜና የሰማን ይመስለኛል። አገር ዉስጥ የሚደረገዉ ትግል ማዕከላዊ አመራር በሚፈልግበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት ኢትዮጵያዊያንን ማሰባሰብ የሚችል ድረጅት መፈጠሩ ሁላችንንም ሊያስደስት የሚገባ መልካም ዜና ነዉ። እኔም ይህንን መልካም ዜና እንደሰማሁ ቁርሴን በላሁና ፌስቡኩ፥ድረገጹና ቲዉተሩ የሚሉትን ለመስማት Internet ፍለጋ ወጣሁ። Internet ቤት ደርሼ አይፎኔን ገና ስክፍተዉ ዜናዉ ሁሉ የሚያወራዉ አዲስ ስለተፈጠረዉ አገር አድን ንቅናቄ ነበር። ለምን እንደሆነ አላዉቅም እኔን ያጋጠመኝ ዜና ግን አዲሱን አገር አድን ንቅናቄ ገና ከመወለዱ “አትደግ” እያለ የሚራገም ዜና ነበር። በፍጹም አልገረመኝም! ምክንያቱም እንዲህ አይነት ከፈረሱ ጋሪዉ የቀደመ ትችት እየሰማሁ ነዋ ያደኩት። ስለዚህ በትዕግስት ማንበቤን ቀጠልኩ። ቆየት ብዬ ነገሮችን በስፋት እያዩና በጥልቀት እያሰቡ የሚጽፉ ሰዎችን ሀሳብ ሳነብ አንድ ነገር ተረዳሁ። በአገር አድን ንቅናቄዉ ስብሰባ ላይ የተነገረዉ ንግግር በሙሉ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ነበር፥ ከእያንዳንዱ ድርጅት ተወካይ አፍ ይወጣ የነበረዉ ቃል የወደፊቷ ኢትዮጵያ የጋራ ቤታችን መሆን አለባት የሚል ተስፋ የሞላበት ቃል ነበር፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የስብሰባዉ መንፈስና የአገር አድን ንቅናቄዉ የተፈጠረበት ዋነኛ አላማ ኢትዮጵያን ከተደቀነባት አደጋ እናድናት የሚል ነበር። እነዚያ ከሀሳባቸዉ ብዕራቸዉ የቀደመ ወገኖቼ የተመለከቱት ግን የጋራ ንቅናቄዉን ይዘትና ይዟቸዉ የተነሳዉን ግቦች ሳይሆን ላይ ላዩን የሚታየዉን የአገር አድን ንቅናቄዉን ቅርጽ ብቻ ነበር። በተለይ አብዛኛዉ ሰዉ የተቸዉ ሶስቱ ድርጅቶች በብሄር የተደራጁ ድርጅቶች የመሆናቸዉን ጉዳይ ነበር። እርግጠኛ ነኝ አሁንም ይህ ስለዚህ ጥንስስ የሚያወራዉ ጽሁፌ ብዙ ጩኸት ይዞብኝ እንደሚመጣ አዉቃለሁ። የሚያወሩ ሰዎች ያዉሩ የሚሉም ሰዎች የሚሉትን ሁሉ ይበሉ – እኔ ግን አንድ የማረጋግጥላቸዉ ነገር አለ – እሱም ድምጽ ፈርቼ ኢትዮጵያን ከአደጋ የሚያድን ሀሳብ ከማፍለቅና ከመናገር በጭራሽ ወደ ኋላ ከማይሉ ኢትዮጵያዊያን ዉስጥ አንዱ መሆኔን ነዉ። “ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነዉ” የሚል አባባል እየሰማሁ ነዉ ያደኩት። ዛሬ ይህንን አባባል ሙሉ ለሙሉ አልቀበለዉም። ያገኘዉን አጋጣሚ አይጠቀምበትም እንጂ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ብቻ ሳይሆን እጁ ላይ ነዉ ያለዉ።
ይህንን መጣጥፍ የሚያነብ አብዛኛዉ ሰዉ ተወልዶ ያደገዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉና ሁሉም ኢትዮጵያን እንዳቅሙ ያዉቃል የሚል እምነት አለኝ። አገራችን ኢትዮጵያ የረጂም ግዜ ታሪክ ያላት አገር ናት። ታሪካችን እንደማንኛዉም አገር ታሪክ መራራና ጣፋጭ ምዕራፎች አሉት። ግን ወደድንም ጠላን መራራዉም ታሪክ ጣፋጩም ታሪክ የኛ ታሪክ ነዉ። ሁለቱንም የታሪክ ምዕራፎቻችንን እንደ ታሪክ መቀበል ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችን ማስተማር አለብን። ኢትዮጵያ ለአዉሮፓ ኢምፔሪያሊዝም እጄን አልሰጥም ብላ የራሷ ብቻ ሳይሆን የአለም ጥቁር ህዝብ የነጻነት ምልክት ሆና የቆየች አገር ናት። ይህ ከምንወደዉና በኩራት ከምንናገረዉ ታሪካችን ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ የበደለዉ ወይም ያገለለዉ ህዝብ አለ ብዬ በፍጹም አላምንም። የተለያዩ የኢትዮጵያ ገዢ መደቦች ግን አንዱን ከፍ ሌላዉን ዝቅ አድርገዉ ህዝብን ከህዝብ መለያየታቸዉንና በህዝብ ላይ ይህ ነዉ ተብሎ ሊነገር የማይችል እጅግ በጣም ከፍተኛ በደልና ሰቆቃ መፈጸማቸዉን ለአንድም ደቂቃ ቢሆን መርሳት የለብንም። ይህ ደግሞ የመራራዉ ታሪካችን አንዱ ክፍል ነዉ። ይህም ታሪካችን በፍጹም ልንክደዉ የማንችለዉ የረጂሙ ግዜ ታሪካችን አካል ነዉና አንገታችንን ቀና አድርገን በግልጽ ልንናገረዉ የሚገባ ታሪክ ነዉ። ከፋም ለማ ልንማርበት የሚገባ ታሪክ እንጂ የምናፍርበትና ከሌላዉ አለም ህዝብ የተለየ ታሪክ የለንም። እንደ አንድ አገር ህዝብ ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን ወደፊት መጓዝ የምንችለዉ ባለፈዉ ታሪካችን ላይ ተመስርተን በዳይና ተበዳይ እየተባባልን ስንካሰስ ሳይሆን የበደለም የተበደለም እንዳለ ተማምነን ይህንን መራራ የሆነዉን የታሪክ ምዕራፍ ላለመድገም ስንማማል ብቻ ነዉ። በታሪክ ነግዶ ብቻዉ ያተረፈ ማንም የለም፥ ብቻዉን የከሰረም የለም። የታሪክ ንግድ ትርፉ ያለፈዉን ስህተት መድገም ብቻ ነዉ። ይህ ደግሞ ማህበረሰባዊ ኪሳራ ነዉ። ዛሬ የሁላችንም አይን አተኩሮ መመልከት የሚገባዉ የትናንቱን በደልና ጭቆና ሳይሆን የነገዉን ብሩህ ዘመን ነዉ። እኛ ማድረግ የምንችለዉ የትናንቱን ስህተት ማረም ሳይሆን ከትናንቱ ስህተት ተምረን ነገን አስተካክሎ መቅረጽ ነዉ። ብዙ ሰዉ ለአገሩ ለኢትዮጵያ ስለሚሳሳ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ በጣም ያስጨንቀዋል። እኔ ተጨንቄም አላውቅ! ተፋቅረን፥ ተስማምተንና ተግባብተን አንድ ላይ ከሰራን የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዳይ እኛ እጅ ላይ እንደሆነ በሚገባ አዉቃለሁ። ታዲያ እጄ ላይ ላለ ነገር ለምን እጨነቃለሁ?
ይልቅ እኔን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ አለመተባበራችንና የምንፈለገዉን ነገር ለማግኘት አንድ ላይ አለመስራታችን ብቻ ነዉ። ብዙዎቻችን ከ”ሀሁ” ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አብረዉን ከተማሩ ብዙ ጓደኞቻችን ጋር ዛሬ በተለያየ ጎራ ተሰልፈን ፍትህ፥ ነጻነትና ዲሞክራሲ ብለን እየታገልን ነዉ። ነገር ግን የእነዚህ የልጅነት ጓደኞቻችን ጥያቄ ከጥያቄያችን አደረጃጀታቸዉ ከአደረጃጀታችን ይለያል። እነዚህን የቀድሞ ጓደኞቻችንን ለምን ከኛ በተለየ መንገድ እንደተደራጁና ለምን ከኛ የተለየ ጥያቄ እንዳነገቡ ማወቅና መረዳት የኛ ግዴታ ነዉ። ስለዚህ እነዚህን ጓደኞቻችንን የምንጠይቃቸዉ ለምን በዘር ተደራጃችሁ፥ ለምንስ የመገንጠል ጥያቄ አነሳችሁ ብለን መሆን የለበትም። ይልቁንም ይህንን ጥያቄ ከመጠያቃችን በፊት እራሳችንን በነሱ ቦታ አድርገን ማየትና ቁስላቸዉ እንዲያሳክከን ሀመማቸዉም እንዲያመን መፍቀድ አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነዉ ህመማቸዉ የሚገባን። ለምን ለሚለዉ ጥያቄም መልስ የምናገኘዉ ያኔ ነዉ። ከኛ በተለየ ጎራ የተሰለፉ ጓደኞቻችን የሚያማቸዉ የታሪክ ሀመም አለ። የህመማቸዉን ፈዉስ አብረን ማግኘት የምንችለዉ እኛን በነሱ ዉስጥ ለማየት ፈቃደኞች የምንሆን ከሆን ብቻ ነዉ። ሌላ ሌላዉ ትርፍ ንግግር ሁሉ የበለጠ ያራርቀናል እንጂ የምንወዳትን የጋራ አገር እንኳን መገንባት ማየትም አያስችለንም።
ይልቅ እኔን የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ አለመተባበራችንና የምንፈለገዉን ነገር ለማግኘት አንድ ላይ አለመስራታችን ብቻ ነዉ። ብዙዎቻችን ከ”ሀሁ” ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ አብረዉን ከተማሩ ብዙ ጓደኞቻችን ጋር ዛሬ በተለያየ ጎራ ተሰልፈን ፍትህ፥ ነጻነትና ዲሞክራሲ ብለን እየታገልን ነዉ። ነገር ግን የእነዚህ የልጅነት ጓደኞቻችን ጥያቄ ከጥያቄያችን አደረጃጀታቸዉ ከአደረጃጀታችን ይለያል። እነዚህን የቀድሞ ጓደኞቻችንን ለምን ከኛ በተለየ መንገድ እንደተደራጁና ለምን ከኛ የተለየ ጥያቄ እንዳነገቡ ማወቅና መረዳት የኛ ግዴታ ነዉ። ስለዚህ እነዚህን ጓደኞቻችንን የምንጠይቃቸዉ ለምን በዘር ተደራጃችሁ፥ ለምንስ የመገንጠል ጥያቄ አነሳችሁ ብለን መሆን የለበትም። ይልቁንም ይህንን ጥያቄ ከመጠያቃችን በፊት እራሳችንን በነሱ ቦታ አድርገን ማየትና ቁስላቸዉ እንዲያሳክከን ሀመማቸዉም እንዲያመን መፍቀድ አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነዉ ህመማቸዉ የሚገባን። ለምን ለሚለዉ ጥያቄም መልስ የምናገኘዉ ያኔ ነዉ። ከኛ በተለየ ጎራ የተሰለፉ ጓደኞቻችን የሚያማቸዉ የታሪክ ሀመም አለ። የህመማቸዉን ፈዉስ አብረን ማግኘት የምንችለዉ እኛን በነሱ ዉስጥ ለማየት ፈቃደኞች የምንሆን ከሆን ብቻ ነዉ። ሌላ ሌላዉ ትርፍ ንግግር ሁሉ የበለጠ ያራርቀናል እንጂ የምንወዳትን የጋራ አገር እንኳን መገንባት ማየትም አያስችለንም።
ብዙዎቻችን እኛ ከምናያትና ከምናስባት ኢትዮጵያ ዉጭ ሌሎች የሚያዩዋትንና የሚያስቧትን ኢትዮጵያን ማየትም ማሰብም አንፈልግም። ይህንን ፍላጎታችንን በሌሎች ላይ እስካልጫንነዉ ድረስ እንደዚህ አይነት አስተያየት መያዙ በራሱ ብዙም ጉዳት የለዉም። አደጋዉና ጉዳቱ የሚታየኝ – እነሱ እራሳቸዉ እጅም ዶማም የሌላቸዉ ሰዎች ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነዉ አደጋ የታያቸዉ ወገኖች አደጋዉን ከወዲሁ ለማቆም ሲወጡና ሲወርዱ “ከእጅ አይሻል ዶማ” እያሉ አላዋቂ ሳሚ ሲሆኑባቸዉ ነዉ። አደራ . . . አትተቹ እያልኩ አይደለም። “መተቸት” ልንለምደዉ የሚገባን “መተቸትም” ሳንወድ በግድ መቀበል ያለብን ከሌሎች ጋር የሚያኖረን እሴት መሆኑን ከልቤ አምናለሁ። ሌላም በጽኑ የማምንበት እሴት አለ – እሱም አንድን ሀሳብ ከመተቸታችን በፊት ሀሳቡን አላምጠን መዋጥ ያለብን መሆኑን ነዉ። አለዚያ ከምንተቸዉ ሀሳብ በፊት ብዕራችን እየቀደመ የምንተቸዉ ትችት እሱ ትችት ሳይሆን የደፈጣ ዉጊያ ነዉ። ዉጊያ ደግሞ ተቺዉንም ተተቺዉንም ይገድላል እንጂ አያስተምርም። ሌላዉ ነገር ደግሞ ተቺዎችን መተቸት እንደሚቻልም መታወቅ አለበት።
እራሳቸዉን በብሄር ተደራጅተዉ ማየት የሚጸየፉ ብዙ ኢትዮጵያዉያን አሉ። መብታቸዉ ነዉ። በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ያለዉ ሰዉ በላ አገዛዝና ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግስታት በህዝብ ላይ በፈጸሙት በደል የተነሳ አንዳንድ ወገኖች ይበጀናል ብለዉ እራሳቸዉን ያደራጁት በብሄር ወይም በዘር ነዉ። እነዚህም መብታቸዉ ነዉ። ሁለቱም ወገኖች እኩል ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ። አንዱን ወገን ከሌላዉ የሚያስበልጥም ሆነ የሚያሳንስ ምንም አይነት መመዘኛ የለም። ኢትዮጵያን ከዘረኛዉ የህወሓት አገዛዝ ነጻ ለማዉጣት፥ አገራዊ አጀንዳ ለመቅረጽና አሁን ያለዉን አገዛዝ የሚተካ የሽግግር መንግስት ለመፍጠር በሚደረጉ ዉይይቶች ሁሉ ላይና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ጉዳይ በሚነሳባቸዉ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ ባለጉዳይ (Stakeholders) ሆነዉ መቅረብ የሚችሉት እነዚሁ እራሳቸዉን በብሄር ያደራጁ፥ ጭራሽ በድርጅት ያልታቀፉና በህብረ ብሄር ድርጅቶች የታቀፉ ሀይሎች ናቸዉ። የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሁላችንም ኢትዮጵያ ሆና መቀጠል የምትችለዉ እነዚህ ሁሉ ሀይሎች አብረዉ በአንድ ጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብለዉ የምትበጃቸዉን ኢትዮጵያ መፍጠር ከቻሉ ብቻ ነዉ። አለዚያ ስራችንና ድካማችን ሁሉ የትናንቱን ስህተት እያወቅን መድገም ይሆናል።
እኛ ኢትዮጵያዉያን እንደ ህዝብ የሚያገናኙን ብዙ የጋራ እሴቶች አሉንና እንመሳሰላለን፥ በማያመሳስሉን ነገሮች ደግሞ እንለያያለን። ለምሳሌ በፖለቲካና በኤኮኖሚ አመለካከታችን እንለያያለን፥ አንዳንዶቻችን ወግ አጥባቂዎች ነን፥ አንዳዶቻችን ደግሞ ለዘብተኞች ነን። አንዳዶቻችን በብሄር መደራጀት እንፈልጋለን አንዳንዶቻችን ጭራሽ ነገራችን ሁሉ በተናጠል መሄድ ነዉ፥ አንዳንዶቻችን ደግሞ ከህብረ ብሄር ድርጅቶች ዉጭ መደራጀት አያምረንም። አንዳንዶቻችን መብት ሲባል የሚታየን የቡድን መብት ብቻ ነዉ፥ አንዳንዶችችን ደግሞ የግለሰብ መብት ከምንም ነገር ይበልጥብናል። ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት አሃዳዊ መንግስት ብቻ ነዉ ብለዉ የሚያምኑ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የለም ኢትዮጵያ ያለፈዉ ታሪኳን መድገም ካልፈለገች በቀር የሚያዋጣት ፌዴራላዊ መንግስት ብቻ ነዉ ብለዉ የሚያምኑ ሰዎችም አሉ። ኢትዮጵያን እነዚህን የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸዉን ሰዎች የምታስተናግድ አገር ማድረግ እንችላለን፥ በዚህች የጋራ አገራችን ዉስጥ እነዚህን እንደ ሁለቱ ዋልታዎች የተራራቁ አስተሳሰቦች ተግባራዊ ማድረግ ግን በፍጹም አንችልም። ስለዚህ አንድ ማድረግ ያለብን የተቀደሰ ነገር ቢኖር እነዚህን የተለያየ አቋም፥ አስተሳሰብና አደረጃጀት ያላቸዉን ሰዎች ማሰባሰብና ተወያይተዉ ወደ አንድ የጋራ ወደ ሆነ ማዕከላዊ ሀሳብ እንዲደርሱ ማድረግ ነዉ እንጂ – በዘር መደራጀት የወያኔን ስህተት መድገም ነዉና በዘር ከተደራጁ ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት ወያኔን መሆን ነዉ እያልን ግማሹን የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት መድረክ ላይ ጥፋ ማለት አንችልም። ደግሞስ እኛ ማነንና ነዉ አንዱን ጋብዘን አንዱን ጥፋ የምንለዉ? እንዲህ አይነት ልዩ መብት የሰጠንስ ማነዉ?
ዛሬ የብዙ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ስጋት አገራችን ኢትዮጵያ ላይ የተደቀነዉ የመበታተን አደጋ ነዉ። ይህ ስጋት ደግሞ ለወያኔ ግዜ በሰጠነዉ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ የሚሄድ ስጋት ነዉ። የሚገርመዉ ይህ ስጋት የወያኔን ዕድሜ ባሳጠርነዉ ቁጥርም እየጨመረ የሚሄድ ስጋት ነዉ። ህወሓት ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻዉን የያዘዉ ስልጣን ከእጁ የሚወጣበት ቀን በተቃረበ ቁጥር ኢትዮጵያን ይበጁኛል ብሎ ለሚያስባቸዉ ሀይሎች እንካችሁ ብሎ በታትኗት ከመሄድ የሚመለስ ሀይል አይደለም። ምንም ነገር ሳንደባበቅ እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ የመበታተን ምንጭ ህወሓት ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያ አንድነት ሽንጡን ገትሮ የሚታገለዉ የግራና የቀኝ አክራሪዉም እንደ ህወሓት አላማዬ ብሎ ባይሆንም በሚያደርጋቸዉና በማያደርጋቸዉ ነገሮች የኢትዮጵያን መበታተን ያፋጥናል። ለምሳሌ መገንጠል አለብን ብለዉ ብረት ካነሱ ሀይሎች ጋር (በብሄር ከተደራጁ ህይሎች ጋር) መነጋገር የለብንም ብሎ የዉይይትና የድርድር በር የሚዘጋ ሀይል ሁሉ የሚሰራዉ ስራ ቢኖር ህዝብን ከህዝብ ማራራቅና የመገነጣጠልን በር መክፈት ብቻ ነዉ። ወደድንም ጠላን አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ሀይሎች አሉ። ኢትዮጵያ በፍጹም መገነጣጠል የለባትም የሚሉ ሀይሎችም አሉ። ኢትዮጵያ እንድትገነጠልም እንዳትገነጠልም የማድረጉ ቁልፍ ያለዉ ሁለቱም ሀይሎች እጅ ላይ ነዉ። ዛሬ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ የሚታየዉ ትልቅ ስህተት አንዱ ወገን አገር አዳኝ ሌላዉ ወገን አገር በታኝ ተደርጎ መታየቱ ነዉ። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገዉ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ከመገነጣጠል አደጋ የሚያድናት የመገንጠል ጥያቄ ያነሳዉ ወገንና ኢትዮጵያ በአንድነቷ መቀጠል አለባት የሚለዉ ሀይል አንድ ላይ ሆነዉ የመፍትሄ ሀሳብ መፍጠር ሲችሉ ብቻ ነዉ። የተናጠል ሩጫዉ የሚያደርሰን ወደምንፈራዉ ቦታ ብቻ ነዉ። ደግሞም አንድን ችግር የምንፈታዉ ችግሩ ለምንና እንዴት እንደተፈጠረ አዉቀን እራሳችንን ችግሩ ከተፈጠረበት ሁኔታ በላይ አድርገን ስንመለከት ብቻ ነዉ። ኢትዮጵያ ትልቅና ሁላችንንም በእኩልነት ማስተናገድ የምትችል አገር ናት። ይህንን የምናምን ሀይሎች ለኢትዮጵያ አንድነት ስንል የምንሰራዉ ስራ ሁሉ ከአጉል ፈሪሳዊነት የራቀ መሆን አለበት። ደግሞም የኢትዮጵያ መገነጣጠል ሁላችንንም የሚጎዳ ነገር ነዉ ብለን እንገንጠል ለሚሉ ሀይሎች የአብረን እንኑር ጥያቄ ማቅረብ ያለብን እኛ እራሳችንን የ”አንድነት ሀይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች ነን። ይህ ሀይል ሆደ ሰፊ ሆኖ የተለያየ አስተሳሰብና የተለያየ አደረጃጀት ካላቸዉ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተገናኝቶ የኢትዮጵያን ችግሮች በጋራ ለመፍታት ፈቃደኛ ባልሆነ ቁጥር ኢትዮጵያ ህመሟ እየባሰበት ይሄዳል እንጂ ፈዉስ አታገኝም። ይህ የ”አንድነት ሀይል” ነኝ ባይ ቡድን እሱ ብቻ ለኢትዮጵያ ተቆርቋሪና እሱ ብቻ የኢትዮጵያ ጠባቂ ነኝ ማለቱን ትቶ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አብሮ መስራት አለበት። ይህንን ማድረግ ከተቻለ ብቻ ነዉ ኢትዮጵያችን ነጻነቷም አንድነቷም ተከብሮ መኖር የምትችለዉ።
ለመሆኑ እኛ እራሳችንን የ“አንድነት ሀይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች “አንድነት” ስንል አንድነት ከማን ጋር ነዉ? የብቻ አንድነት አለ እንዴ? ወይስ እግዚአብሄር የእስራኤልን ልጆች መርጦ ህዝቤ እንዳላቸዉ እኛም እየመረጥን ኢትዮጵያዊ የምናደርገዉና የማናደርገዉ ህዝብ አለ? ደግሞስ ይህንን ለማድረግ እኛ ማነን? ማነዉ የዚህ ዘመን ቄሳር ያደረገን? ትዝ ይለኛል ኮሎኔል መንግስቱ ኢትዮጵያ ከእጁ እየወጣች ስትሄድ- ኢትዮጵያ ልትሞት ነዉ. . . ኡኡ፥ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይም ሞት . . .ኡኡ፥ ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር . . .ኡኡ እያለ ጆሯችንን ያደነቁር ነበር። ዛሬም አማራዉ ሊያልቅ ነዉ . . .ኡኡ፥ ኦሮሞ ተጨፈጨፈ . . .ኡኡ፥ ኢትዮጵያ አለቀላት . . .ኡኡ የሚለዉ ጩኸት በየቦታዉ እየተስተጋባ ነዉ። የመንግስቱ “ኡኡ” መንግስቱን ወደ ዚምባቡዌ ከመፈርጠጥ እንዳላዳነዉ ሁሉ የዛሬዉም የኛ “ኡኡ” አማራን ከዕልቂት ወይም ኦሮሞን ከጭፍጨፋ አያድነዉም።አማራዉንም ኦሮርሞዉንም ባጠቃላይ ኢትዮጵያን ከጥፋት የሚያድናት ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኦሮሞ “አማራዉ ወገኔ ነዉ” አማራዉም “ኦሮሞ ወንድሜ ነዉ” እያለ የሚጮኸዉን ድምጽ በጥንቃቄ ስንሰማና ለዚህ ድምጽ ድርጅታዊ ምላሽ ስንሰጥ ብቻ ነዉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በየትኛዉም መልኩ የተደራጀዉን ኢትዮጵያዊ ማቀፍ እንጂ ማግለል የለብንም። ከዚህ በተረፈ አማራዉ ለፍትህ፥ ለነጻነትና ለእኩልነት የሚያደርገዉን ግዙፍ ትግል “ለአማራነት” ብቻ የሚደረግ ትግል ማስመሰልና ከአንድ አመት በላይ የፈጀዉንና የአያሌ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ ሰቅዞ የያዘዉን የኦሮሞ ህዝብ ተጋድሎ የኦሮሞ ብቻ ለማድረግ የሚደረገዉ ሩጫ አማራዉንም፥ ኦሮሞዉንም ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ተራ በተራ ያስጨፈጭፋል እንጂ ሌላ ምንም ፋይዳ የለዉም። ከሁሉም በላይ ደግሞ አገር ቤት ዉስጥ ያሉት የኦሮሞና የአማራ ወገኖቻችን እየተናገሩ ያሉት አንድነታቸዉን ነዉ እንጂ ለየብቻ መሆናቸዉን አይደለም። የኛ ተግባር ይህንን የአንድነት ድምጽ መደገፍ ነዉ እንጂ በምንም አይነት የራሳችን አጀንዳ ሊኖረን አይችልም . . . . አይገባምም! የአገራችን የኢትዮጵያ አንድነት ፈተና ላይ መዉደቁን ሁላችንም እያየን ነዉ። ይህንን አደጋ ላይ የወደቀ አንድነት ሙሉ ለሙሉ ጠግነን የኢትዮጵያን አንድነት የምናረጋግጠዉ “አንድነታችንን” አደጋ ላይ ጥለዉታል ብለን ከምናስባቸዉ ሀይሎች ጋር በመደራደር ነዉ። ይህንን ለማድረግ ደግሞ እራሳችንን የአንድነት ሀይሎች እያልን የምንጠራ ወገኖች ነን በዘር የተደራጁ ወገኖቻችን ያሉበት ቦታ ድረስ ሄደን እንደራደር ብለን የመጀመሪያዉን እርምጃ መዉሰድ ያለበን። ባለፈዉ ወር ዋሺንግተን ዲሲ ዉስጥ ያየነዉ ይህንኑ መልካም ጅምር ነዉና ይህንን ጅምር እደግ ተመንደግ ልንለዉ ይገባል።
እቺ እናታችን ብለን የምንጠራት ኢትዮጵያ የሁላችንም እናት ናት። ኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ደሴት የመሆኗን ያክል የክርስትናና የዋቄፈቻ እምነት ተከታዮችም ደሴት ናት። ኢትዮጵያ የኦሮሞዎች አገር በሆነችዉ ልክ የአማራዎች፥ የሱማሌዎች፥ የትግሬዎችና የሌሎችም ብሄር ብሄረሰቦች አገር ናት። እኛ እራሳችንን የ”አንድነት ሀይሎች” ብለን የምንጠራ ወገኖች ኢትዮጵያ ላይ አለን የምንለዉ ባለቤትነት እራሳቸዉን በብሄር ያደራጁ ወገኖቻችን ካላቸዉ ባለቤትነት ቤሳ ቤስቲን አይበልጥም አያንስምም። ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያዊያን ነን። ስለዚህ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሁሉ ማንም ሰዉ ወይም ቡድን ከላይ ሆኖ ጋባዥና ከልካይ መሆን የለበትም- ሊሆንም አይችልም! ኢትዮጵያዊ
የሚያደርገን የተደራጀንበት መንገድ፥ የምንናገረዉ ቋንቋ ወይም የምንከተለዉ ሀይማኖት አይደለም። ኢትዮጵያዊ የሚያደርገን ብዙ ዝርዝር ዉስጥ ሳንገባ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ዉስጥ ተወልደን ማደጋችን ብቻ ነዉ።
እስኪ እግዜር ያሳያችሁ እኛ የአንድነት ሀይሎች የምንባል ሰዎች እንዴት አድርገን ነዉ እኛ ከተደራጀንበት መንገድ ዉጭ የተደራጀዉን ኢትዮጵያዊ አግልለን የኢትዮጵያን አንድነት ከመፍረስ የምናድነዉ? የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ ወደቀ ማለት አንዳንድ ወገኖች ከኢትዮጵያ የመገንጠል ጥያቄ አነሱ ማለት አይደለም እንዴ? ታዲያ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ተቀራርበንና ህመማቸዉን ተጋርተን ለሁላችንም የምትስማማ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የምናደርገዉ ጥረት ለምንድነዉ እንደ ሐጢያት የሚታየዉ? ጥረት የሚያደርጉት ወገኖችስ ለምድነዉ እንደ ማሪያም ጠላት የሚታዩት? በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ ካነሱ ወገኖች ጋር ካልተቀራረብንና ካልተወያየን ከነማን ጋር ነዉ የምንወያየው? ከእነዚህ ወገኖች ጋር ሳንገናኝ እንዴት አድርገን ነዉ የኢትዮጵያን አንድነት የምናረጋግጠዉ? . . . በሀይል? . . . .በስድብ? . . . በዛቻ? እሱንማ ስንት አመት ሞክረን ዉጤቱ ምን እንደሆነ አየነዉኮ! ምነዉ ጃል ካለፈዉ ስህተታችን አንማርም እንዴ?
ህወሓትንና ድህነትን የመሳሰሉ ሁለት ግዙፍ ጠላቶች ፊት ለፊታችን ላይ ተገትረዉ የኛ እርስ በርስ መባላት ዉጤቱ ሌላ ሶስተኛ ጠላት መፍጠር ብቻ ነዉ። ስለዚህ ዛሬና በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ዉስጥ ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀዉ ትልቁ ስራ የትኛዉን ስትራቴጂ፥ ዬትኛዉን ስልትና የትኛዉን ሀሳብ ብንከተል ነዉ የታሪክ ስብራታችንን ጠግነን፥ መከፋፈላችንን አስወግደንና አንድነታችንን አጠናክረን የወደፊቷን ፍትህ፥ ዲሞክራሲና እኩልነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለዉ የሚለዉን ቁልፍ የዘመናችን ጥያቄ መመለስ ነዉ። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እነ እገሌ ከዬት ነዉ የመጡት፥ እነ እገሌ እንዴት ነዉ የተደራጁት ወይም እነ እገሌ ሀይማኖታቸዉ ምንድነዉ እያልን ከሆነ የምንሰባሰብዉ እራሳችንን ከመሰረታዊ የሰዉ ልጆች ማንነት በታች አስመዝግበንና የማይሽር የታሪክ ጠባሳ ለልጅ ልጆቻችን ትተን ወደዚህ አለም “መጥተዉ ሄዱ” ተብሎ ይነገርልናል እንጂ የአገራችንን ችግር አንፈታም። የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ከችግሮቿ በላይ መሆን አለብን። ይህ ደግሞ መደማመጥን፥ መከባበርን፥ መተማመንን፥ሰጥቶ መቀበልን፥ የሌላዉን ቁስል መረዳትን፥ መናበብንና አንዱ ለሌላዉ ማሰብን ይጠይቃል። ይህንን ማድረግ ከቻልን አገራችን ኢትዮጵያን ትልቋ የጥቁር ህዝብ ደሴት ማድረግ እንችላለን። ይህንን ማድረግ እንድንችል ቸሩ እግዚአብሄር ይርዳን። አሜን!!!! ቸር ይግጠመን።
ህወሓትንና ድህነትን የመሳሰሉ ሁለት ግዙፍ ጠላቶች ፊት ለፊታችን ላይ ተገትረዉ የኛ እርስ በርስ መባላት ዉጤቱ ሌላ ሶስተኛ ጠላት መፍጠር ብቻ ነዉ። ስለዚህ ዛሬና በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ዉስጥ ከእኛ ከኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀዉ ትልቁ ስራ የትኛዉን ስትራቴጂ፥ ዬትኛዉን ስልትና የትኛዉን ሀሳብ ብንከተል ነዉ የታሪክ ስብራታችንን ጠግነን፥ መከፋፈላችንን አስወግደንና አንድነታችንን አጠናክረን የወደፊቷን ፍትህ፥ ዲሞክራሲና እኩልነት የተረጋገጠባትን ኢትዮጵያን መገንባት የምንችለዉ የሚለዉን ቁልፍ የዘመናችን ጥያቄ መመለስ ነዉ። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ እነ እገሌ ከዬት ነዉ የመጡት፥ እነ እገሌ እንዴት ነዉ የተደራጁት ወይም እነ እገሌ ሀይማኖታቸዉ ምንድነዉ እያልን ከሆነ የምንሰባሰብዉ እራሳችንን ከመሰረታዊ የሰዉ ልጆች ማንነት በታች አስመዝግበንና የማይሽር የታሪክ ጠባሳ ለልጅ ልጆቻችን ትተን ወደዚህ አለም “መጥተዉ ሄዱ” ተብሎ ይነገርልናል እንጂ የአገራችንን ችግር አንፈታም። የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ከችግሮቿ በላይ መሆን አለብን። ይህ ደግሞ መደማመጥን፥ መከባበርን፥ መተማመንን፥ሰጥቶ መቀበልን፥ የሌላዉን ቁስል መረዳትን፥ መናበብንና አንዱ ለሌላዉ ማሰብን ይጠይቃል። ይህንን ማድረግ ከቻልን አገራችን ኢትዮጵያን ትልቋ የጥቁር ህዝብ ደሴት ማድረግ እንችላለን። ይህንን ማድረግ እንድንችል ቸሩ እግዚአብሄር ይርዳን። አሜን!!!! ቸር ይግጠመን።
ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር emadebo@gmail.com
No comments:
Post a Comment