Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, November 15, 2016

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ ካናዳ ጠየቀች


ኢሳት (ህዳር 5 ፥ 2009)
ሰሞኑን የካናዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስቴፋኒ ዲዮን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ተከትሎ ሃገሪቱ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓቱ ማሻሻያ እንዲደርግበት ጥሪን አቀረበች።
በሚኒስትሩ ዲዮን የተመራ የልዑካን ቡድን ባለፈው ሳምንት ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ማካሄዱ ይታወሳል።
በሁለቱ ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል የተካሄደውን ውይይት ተከትሎ መግለጫን ያወጣው የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፖለቲካ ስርዓቱ ማሻሻያ በተጨማሪ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ሰላማዊ ውይይት እንዲካሄድም ማሳሰቡን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
የካናዳው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዛቸው አስቀድሞ ሁለት ታዋቂ የሃገሪቱ የምክር ቤት አባላት ሃገራቸው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን እንድታደርግ ዘመቻ መክፈታቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስጋት እንዳሳደረባቸው የሚገልጹት የካናዳ የፓርላማ አባላት፣ የሃገራቸው መንግስት ለኢትዮጵያ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ግምት ውስጥ በማስገባት ለሰብዓዊ መብት መከበር ቅድሚያን እንዲሰጥ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ከፓርላማ አባላቱ የቀረበው ቅሬታ ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የካናዳው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቲር ስቴፋኒ ዲዮን በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካ የፖለቲካ ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር መምከራቸው ታውቋል።
በሁለቱ ባለስልጣናት መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ ውይይቶች መካሄዳቸውን ያወሳው የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትርጉም ያለውና የሃገሪቱ ወጣቶችን ተሳታፊ ያደረገ የፖለቲካ ማሻሻያ ያለምንም መዘግየት ተግባራዊ መደረግ እንዳለበት አመልክቷል።
የካናዳ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ መደረግ ተከትሎ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ሲል በተደጋጋሚ ስጋቱን ሲገልጽ ቆይቷል።
ከካናዳ መንግስት በተጨማሪ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረትና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ያባብሳል ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials