Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, November 20, 2016

በብሄር የተዋቀረ ፓለቲካ አደረጃጀት የኢትዮጵያን የፓለቲካ ችግር ሊፈታ አይችልም – ከደመቀ ገሰሰ (PhD)


በብሄር የተዋቀረ ፓለቲካ አደረጃጀት የኢትዮጵያን የፓለቲካ ችግር ሊፈታ አይችልም – ከደመቀ ገሰሰ (PhD)


የብሄር ፓለቲካ ማለት በአንድ ብሄር ወይም ዘውግ ለምሳሌ አማራ፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣ጉራጌ፣ሶማሌ፣ወዘተ በሚሉ ብሄርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ አደረጃጀት ማለት ነው። ይህ የፓለቲካ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ታሪክ በተግባር ላይ የዋለው የትግራዮ ነፃ አውጪ ድርጅት ህወዓት በ1983 አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢህዴግ በሚባል ብሄር ተኮር የፓለቲካ ፓርቲወች ጥምረት በመመስረት ነው። ምንም እንኳ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሄሮች ያሉበት አገር ቢሆንም የስልጣን በትሩን በበላይ በሚያዝዘው የትግራዮ ህወዓት የብሄር ፓለቲካ ፓርቲ በሚመቸው መልኩ ያለምንም የህዝብ ተሳትፎ ከ54 በላይ ብሄሮች የሚኖሩበት ደቡብ ኢትዮጵያን “ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች” በሚል ስብስብ ውስጥ በመክተት የሶማሌ፣የሃረር፣የትግራይ፣የአማራ፣-የጋምቤላ፣የቤንሻንጉል ጉምዕዝ፣የአማራ እና የኦሮሞ የብሄር ፓለቲካ ብቻ ሳይሆን እኒህ የብሄር ፓለቲካ ፓርቲወች የሚያስተዳድሩት ጂኦግራፊያዊ ክልልም በመወሰን የተከናወ ነው።

እንግዲህ የብሄር ፓለቲካ ቋቅ እስኪለን 25 ዓመታት ተግተነው የመጣ ለውጥ ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እራሱን ይጠይቅ።

ይህ የብሄር ፓለቲካ ገና ከጅምሩ በብጥብጥ እና በዘር ፉጅት ነው ሃሁ ያልነው። የእኛ ክልል በሚሉት ውስጥ ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ አማራወችን በመጨፉጨፉ እና በማባረር ተጀመረ። ይህ እስካሁን እልባት ያላገኘ ችግር ሆኖ ቀጥሏል። ከጉራፈርዳ፣ከአፋር፣ሶማሌ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ በቅርቡ ደግሞ በጌዲዬ ዞን የሆነውን አይተናል።

እንግዲህ በብሄር የተደራጀ የፓለቲካ ፓርቲ በመሰረቱ የሚያደላው ለሚወክለው ብሄር ነው። ይህ በግልፅ የታየ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳ በርካታ ሚሊዮን አማራወች እና ሌሎች ብሄሮች ኦሮሚያ ውስጥ ቢኖሩም የኢህዴግ ብሄር ፓለቲካ ግን እንኳን የፓለቲካ ተሳትፎ እድል ሊሰጣቸው ይቅርና በኦሮሚያ ሲቭል መስሪያ ቤቶች በቅድሚያ ስራ ለማግኘት ኦሮሞ ልትሆን ግድ ይላል። በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ ችግር ነው። የክልሉ ትምህርት በኦሮምኛ ይሰጥ ብሎ ሲል በርካታ የሌሎች ብሄሮች ልጆቻቸው በቋንቋቸው እንዳይማሩ ተፈረደባቸው። ይህ ምን አይነት ፉትሃዊነት እንደሆነ አስረዱኝ?

ወያኔን የሚኮንኑ የብሄር ፓለቲካ ፓርቲወች ወያኔን የሚከሱበት ትልቁ ክስ የብሄር ፓለቲካው የይምሰል ነው በማለት ነው። ይህም ማለት ኦሮሞ ክልል ለኦሮሚያ፣ሶማሌ ለሶማሌወች ፣ወዘተ መሆን አለበት ነው የሚሉት። ህወዓት በሞግዚትነት የሚመራን ነገር ይቅር ነው የሚሉት። ነገር ግን እነዚህ በብሄር የተደራጁ ተቀዋሚ የፓለቲካ ፓርቲወች ወያኔ ቢወርድ እነርሱ የእኛ ብለው በሚጠሩት ክልል ውስጥ አገሬ ብለው ለሚኖሩት ሌሎች ወገኖች መፉትሄ የሚሰጥ አማራጭ ሲያቀርቡ አይታይም። የሚሉት ሙሉ በሙሉ ትግራይ ክልል ለትግሬ፣ ኦሮሞ ክልል ለኦሮሞ፣ሶማሌ ክልል ለሶማሌ ወዘተ ነው።

ሌላው ትልቅ ችግር ይህ የብሄር ፓለቲካ ከ13% በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ድብልቅ ህዝብ የሚወክለው ፓርቲ አይኖርም ማለት ነው።

ኢትዮጵያ ምድሬ፣ አገሬ፣ አፈሬ ናት ብሎ እትብቱ የተቀበረበት መሬት የአንተ አይደለም እየተባለ በብሄር ፓለቲካ ስም የሚደርስበትን እያየን ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አገር ስትመሰረት ተለያይተው ይኖሩ የነበሩ አገሮች በፌደሬሽን አልያም በሃይል አንድ ላይ ተጨፉልቀው አይደለም። የአውሮፓ ቅኝ ገዥወች ወደ አፉሪካ ከመምጣታቸው በፊት ኢትዮጵያ ጥንት የነበረች ታሪካዊ አገር ነች። ይህ ማለት የትኛውም የኢትዮጵያ መሬት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ቅድመ-አያቶች ደም እና አጥነት ተጠብቆ የኖረ አገር ነው። መቼም ፈጣሪይ ከላይ ይህ ላንተ፣ያኛው ለዚያ ብሎ ከልሎ የሰጠን የግዛት መሬት የለም። ሁሉም አገሮች እንደ አገር ሲመሰረቱ እንደሆነው ቅድመ-አያቶቻችን ከደርቡሾች፣’ከጣሊያን ጋር፣ከእንግሊዝ ፣ከኦቶማን ቱርኮች እና ከሌሎች ጋር እየተፋለሙ ያቆዮልን በጋራ ደም እና አጥንት የተከበረ የጋራ አገር ነች ኢትዮጵያ።

ጣሊያን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በሽንፈት የወጣበትን የአድዋን ቂም ለመበቀል በሁለተኛው አለም ጦርነት ዋዜማ ወቅት ኢትዮጵያን ዳግም ወሮ ለአምስት አመት ሲቆይ ይቺን ተከብራ የኖረችውን አገር ከፉፈሎ ለመግዛት እና ለማዳከም ዛሬ ላይ ወያኔ የተጠቀመበትን የብሄር ካርታ በመስራት አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳ ተንኮል በመሸረብ ትልቅ የክፋት ስራ ሲሰሩ ቆይተው በእንግሊዝ እርዳታ ኢትዮጵያን የመውረር ህልማቸው እውን ሳይሆን ቀረ።

ወያኔ በ1983 ዓም ወደ ስልጣን ማማ ሲመጣ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ለማፉረስ የሰራውን የብሄር ካርታ አቧራ አራግፈው እየው ዛሬ ለደረስንበት ውድቀት ዳረጉን።

ወገኖቼ

ይህ የብሄር ፓለቲካ በኢትዮጵያ ውስጥ ከእልቂት እና እርስ በእርስ ግጭት ውጭ ምንም መፉትሄ እንደማይኖረው አንድ አንድ ነገሮችን እያነሳን እንነጋገር።

የብሄር ጂኦግራፊያዊ አከላለል በብዙ መልኩ መዘዙ የከፋ ነው። ለምሳሌ ወያኔ በስራው የአማራ ክልል ውስጥ ብናይ በአማራ ክልል ውስጥ ከአማራ ብሄር ውጭ የሆኑ ቅማንት፣ኦሮሞ፣ትግሬ፣አገው፣ወዘተ ብሄሮች ይኖራሉ። ደቡብ ክልል ብቻ ከ54 በላይ ብሆሮች አሉ። በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በርካታ ሌሎች ብሄሮች አሉ። በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ እውነታ ነው ያለው።

እንግዲህ እስካሁን ባየነው የብሄር ፓለቲካ በየክልሉ ላሉት ሌሎች ብሄሮች እኩል መብት የሚሰጥ ፉትህዓዊ የሆነ አሰራር የለም ወይም ደግሞ እኒህ ብሄሮች የራሳችን ክልል ይኑረን ጥያቄወች ተደፉጥጠው እንጂ ጥቄቃወችን ያነሳሉ።

ሌላው እያንዳንዱ የብሄር ክልል የእራስን እድል በራስ የመወሰን መብቱ ይጠበቅልን ካለ የክልሉ አከላለል በራሱ ፉትሃዊ አይደለም። ቀድሜ ያነሳውትን ታሪክ እዚህ ላይ ለማስታወስ ኢትዮጵያ የዛሬዋን ጂኦግራፊያዊ ቅርፅ እንድትይዝ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምሮ እስካሁኗ እለት በእኩል ደም እና አጥንት የተጠበቀ ነው። ይህ ከሆነ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሚደረገው የክልል አከላለል እኩል ባለቤትነት ሊኖራቸው ግድ ይላል። ለምሳሌ የዛሬው ደቡብ ህዝብ ወይም ኦሮሚያ ክልሎች ከጥንት ጀምሮ የሰሜኑም ፣ምስራቁም ፣መካከለኛው ኢትዮጵዊ አብሮ ዋጋ ከፉሎ እንደ አገር ባይቆይ ኖሮ ይህ አካባቢ ወይ ኬንያ አልያም ሱዳን በሆኑ ነበር። ስለዚህ የአፋር ህዝብ ወይም የትግራይ ህዝብ አሁን ባለበት ትንሽ እና ደረቃማ ቦታ ብቻ ይወሰን ካልን ፉትሃዊነቱ ምን ላይ ነው?

ለዚህ ነው የብሄር ፓለቲካ በፉፁም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት የማያመጣው። ይህ የብሄር ፓለቲካ መቼውንም ቢሆን ችግራችንን ይበልጥ ውስብስብ እያደረገው ከመሄድ ውጭ መፉትሄ ሊሆን አይችልም።

ስለዚህ ብቸኛው መፉትሄ በብሄር ሳይሆን በዜግነት ብቻ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓለቲካ አደረጃጀት ነው። የግለሰብ መብት ላይ ትኩረት ያደረገ የዴሞክራሲ ስርዓት ብቻ ነው የተረጋጋች አገር የሚመሰርተው። ይህን የሳተ የስሜት ፓለቲካ ለጊዜው ይምሰለን እንጂ መዘዙ እጅግ ከባድ ነው።

ማስተዋልን አብዝቶ ይስጠን
አሜን!

1 comment:

  1. ወዳጄ ኮክተር ደመቀ ያሰፈርከውን መልክት አንብቤ ስቅሰቅ ብሎ ማልቀስ እስኪያምረኝ ድረስ ነው ሆድ የባሰኝ
    ዘላቂ የፖለቲካ መፍትሄ ለህዝባችን የሚያመጣው፣ በጣም ትክክለኛ እና ለኢትዮጵያ የሚያስፍልጋት ቅንነት የተሞላው እይታህ የሚደነቅ ነው።
    እውነተኛው መንገድ የግለሰብን መብት መሰረት ያደረገ ዲሞክራሲ ሆኖ ሳለ፤ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንዱ ብሄር ሌላውን ብሄር እየሰደበ በቡድን ታግሎ የራሱን የበላይነት ለማስፈን ሲፈራገጥ ማየት እጅግ አስነዋሪው የትግል ስልት መሆኑን ብዙዎቻችን እንረዳለን ብየ አምናለሁ። ሆኖም ግን የት ይደረሳል?
    ወተት የለም እንጂ ዳቦማ ቢኖር ጥሩ ቁርስ በልተህ ትሄድ ነበር። ይላል አንድ የልጅነት ጓደኛየ የሚሰራው ግራ ሲገባው።
    ማለት የፈለኩት እሄን በብሄር የተዋቀረ ክልልና ፌደሬሽን መንካት የሕገመንግሥት ጥሰትና አገር ማፍረስ ነው በሚል ማስፈራሪያ ተስፋ ቆርጠው አንዳንዶች ፖለቲካውን ጨርሰው ሲተውት፤ ጥቂቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ጠላቶች ባሰመሩልን የብሄር መስመር መንጎዱን ተያይዘነዋል።
    ሰው ባለው ይሸናል እንደሚሉት መሆኑ ነው!
    ግራ የተጋባውን ፖለቲካ የሚያስተካክል አንድ ደፋር ሰው እስኪመጣ ድረስ በዚሁ መቀጠላችን የማይቀር መሆኑን ሳስብ በጣም እያዘንኩኝ፤ ማስተዋል ይስጠን ሳይሆን በአዲስ ራዕይ ቀድሞ የሚወጣ ሰው ይስጠን እላለሁ።

    ReplyDelete

wanted officials