Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, November 4, 2016

ፓርላማው ይበተን! ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ!


ፓርላማው ይበተን! ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ!

በህይወቴ በኢትዮጵያ ሶስት መንግስት የማየት ዕድል አጋጥሞኛል። ሶስቱም መንግስታት አገዛዛቸውን የሚፈታተን ተቃውሞ ከህዝብ ጠንከር ብሎ ሲመጣባቸው የተጠቀሙት የፕሮፓጋንዳ ስልት ተመሳሳይነት በጣም አስገራሚ ነው። አጼ ሃይለስላሴ ስልጣናቸው ከላይ ከፈጣሪ የመጣ ነው ብለው ያምኑ የነበረ፣ መንግስቱ ሃይለማርያም የኮምኒስት ፓርቲ መሪ ነኝ ይል የነበርና፣ ያሁኖቹ ኢህአዴጎች ደግሞ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ደቀ መዘሙራን ነን ባዮች፣ የህዝብ ተቃውሞን አስመልክቶ የሚከተሉት የማጥላላት ፕሮፓጋንዳቸው መመሳሰል፣ ምናልባት ቤተ መንግስቱን ባለ ተራ ሆነው ለሚይዙት ቀድሞ የተዘጋጀ የሚሞሉት ሰነድ ይኖራል የሚያስብል ነው። ሶስቱም ስርዓቶች የህዝብ ትግል ጠንከር ብሎ ሲመጣ ወደ ራስ በመመልከት፣ የችግሩን ምንጭ ፈልጎ ለህዝቡ አጥጋቢ መልስ በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ከመሞከር ይልቅ፣ ህዝቡ የራሱን ፍላጎትና መብት የማያውቅ፣ በውጭ ሃይሎችና ለውጭ ሃይሎች ያደረና ፣የነሱን ሃገር አፍራሽ ተልዕኮም ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀስ ሃይል አድርገው ጧት ማታ የፕሮፓጋንዳ ተጠቂ ያደርጉታል። በአጼው ጊዜ፣ የሶሻሊስት አገሮችና አረቦች ፣ በደርግ ዘመን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የአረብ አድህሮት ሃይሎች፣ በህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ግብጽና ኤርትራ ለዚህ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የዋሉ ሃይሎች ናቸው። ህዝብ ትዕግስቱን ጨርሶና ጭቆና አስመርሮት ሲነሳ፣ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ፣የገዢዎች አሰልቺ የማጥላላት ዘመቻዎችም ሆነ እስርና ግድያ ሳይበግረው፣ በበለጠ እልህ ትግሉን ጠበቅ እንደሚይደርግና በሰተመጨረሻም፣ ገዢዎቹን መንግሎ እንደሚጥል በሁለቱ መንግስታት ያየነው ጉዳይ ነው። የህወሃት ቁንጮዎች ከታሪክ የመማር እምቢተኝነት ካሳዩ፣ ይዋል ይደር እንጂ እጣ ፈንታቸው ከቀደሟቸው መንግስታት የተለየ አይሆንም። ኢትዮጵያን ባለፉት ጥቂት አመታትና በተለይም ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በማናወጥ ላይ ያሉት የህዝብ እንቅስቃሴዎች ስፋት ባለው የሀገሪቷ ክፍሎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከበተናጠል መጠቃት ትምህርት የወሰደው ህዝብ ትግሉን የማቀናበር ፍንጭ ማሳየቱ፣ ስልጣን ላይ ላለው የህወሃት ቁንጮ ቡድን፣ ለስርዓቱ ማብቃት ማንቂያ ደወል በመሆኑ ትግሉን ለማጨናገፍና ለመምታት ሙከራው ሁሉ ቢከሽፍበት፣ በስተመጨረሻ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ ሁለት ሳምንት አልፎታል። በዚህ የጥፋት አዋጅ አማካይነትም፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በእስር በማጎርና ፣በርካቶችን በመግደል፣ ለእስር ያልተዳረጉትን ደግሞ ነገ እገደል ወይ እታሰር በሚል ስጋት ጨምድዶ በመያዝ መላ ሃገሪቱን ወደ አስከፊ እስር ቤት ለውጠዋታል።ይሄ ስብዓዊ መብትን አስመልክቶ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው በአስር ቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ኪሳራ ደግሞ ለረጅም ጊዜ አገራችንን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል መሆኑ ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈልግከውን ፓርቲ/ሰው የመምረጥ ሙሉ መብት አጎናጽፈንሃል ብለው ሲምሉ ሲገዘቱ የከረሙት የህወሃት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች ስልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ በተካሄዱ፣ የከተማ፣ የክልሎችም ሆነ ሃገራዊ ምርጫዎችን ግን ከድጡ ወደማጡ በሆነ አካሄድ ምርጫዎችን ሁሉ ሲያጭበረብሩ ከርመው፣ ይባስ ብለው ባለፈው 2007 ምርጫ ጭርሱኑ መቶ በመቶ አሸንፈን መንግስት መስርተናል በሚል መሪር ፌዝ የሀገራችንን ህዝብ ከማሳዘናቸውም በላይ ፣ ኢትዮጵያን በምርጫ ስም ከሚቀልዱ የአለም አምባገነኖች ተርታ የአንደኛነቱን ስፍራ እንድትይዝ አድርገዋታል። ግንቦት 2007 ተካሄደ የተባለው ምርጫ በምንም መመዘኛ ተአማኒነት ሊኖረው እንዳልቻለ መቶ በመቶ አሸንፈናል ባሉ ማግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ባካሄደው ትግል ስለታየና፣ በአለምም ፊት እንዳዋረዳቸው በመገንዘብ የህወሓት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች አዲስ ትርክት ፈጥረው ተራ አጭበርባሪነት ሲያካሂዱ ከርመዋል። በጠቅላይ ምኒስትሩ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ በውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም፣በአማካሪው በረከት ስምኦንና በሌሎች ቦዘኔ ምሁራን አማካይነት “መቶ በመቶ አሸነፍን እኮ ስንል ሁሉንም ድምጽ አግኝተናል በሚል መልኩ ሳይሆን፣ የምርጫ ህጉ በሚያዘው መሰረት አብላጫውን ድምጽ በማግኘታችን ነው የፓርላማውን ሁሉንም ወንበር ያሸነፍነው” “ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙ በመሆናቸውና ተቀናጅተው መወዳደር ባለ መፈለግ በተናጠል ባደረጉት ፉክክር እንደ ቅርጫ የህዝቡን ድምጽ በመከፋፈላቸው ለኛ ባብላጫ ድምጽ መቶ በመቶ እንድናሸንፍ በር የከፈቱልን…” ወዘተ የሚሉ ተራ ቅጥፈቶች፣ ለሃገር ቤትና ለውጭ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሲያስተጋቡ ሰምተናል። እውነቱ ግን የግንቦቱ ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ስም እንደ አንድ የኢህአዴግ መስሪያ ቤት የሚንቀሳቀሰው ይሄ ተቋም ሰኔ 2007 ባወጣው ሪፖርት መሰረት፣ ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ 95.05% የህዝብ ድምጽ በማግኘት የክልሎችንም ሆነ የፌዴራል ፓርላማ መቀመጫዎችን መቶ በመቶ እንዳሸነፉ መለፈፉ ነው።




የህዝቡ ትግል ጠንከር ሲል ሰሞኑን ለማደናገር በማሰብ ዘፈናቸውን ለውጠው ችግሩ የምርጫ ህጉ ላይ ያለ ለማስመሰል፣ ለመጭው ምርጫ አብላጫ ድምጽ ያገኘ ያሸንፋል የሚለውን ህግ አሻሽለን ተመጣጣኝ ውክልና በሚል እንደርገዋለን የሚል መጀመሪያ በበረከት ስምኦን እንደ አንድ አማራጭ፣ በኋላ ደግሞ ፕሬዘዳንቱ ለፓርላማው ባደረገው አመታዊ ንግግር ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ይፋ አድርገዋል። ህዝብ ግን ምርጫውን አስመልክቶ ያለው መሰረታዊ ችግር፣ ህጉ ሳይሆን የህወሓት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች የአምባገነንነት አባዜና ይሀንን ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ያቋቋሟቸው ፣እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት መሆናቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ለዚህም ነው ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ይቋቋም ፓርላማው ይበተን፣ አዲስ አገራዊ ምርጫ ይካሄድ ወቅታዊው ጥያቄ የሚሆነው። “ሕዝብ አለቃችን ነው” የሚል መፈክር በየቦታው በመለጠፍ፣ ዳግማዊ ጥልቅ ተሃድሶ አካሂደን ከመበስበስ ጸድተን፣ የህዝብ አገላጋይነታችንን አንደገና አናስመሰክራለን በማለት ደጋግሞ በመለፈፍ ህዝብን ማታለል ጊዜው ያለፈበት መሆኑን በመገንዘብ፣ የህዝብ ትግል ወቅታዊ ያደረገውን “ፓርላማው ይበተን ” (ሃቀኛ የህዝብ ተወካዮች አይደሉምና !) ” ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ” (ያምናውን ምርጫ መቶ በመቶ አሽንፈናል የሚለው መቶ በመቶ ቅጥፈት ነውና!) በጸጋ ተቀብሎ ተግባራዊ ከማድረግ ውጭ አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ መውጫ ሌላ መንገድ የለም:: ፓርላማው ይበተን ! ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ! የሚለው የህዝብ ጥያቄ በማያሻማ መንገድ መቅረቡን የተረዱት የህወሃት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች የቀድሞ ቃል አቀባያቸው ጌታቸው ረዳን ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጥ በመላክ ለዚህ የህዝብ ጥያቄ ጊዜያዊ እምቢተኝነታቸውን አሳውቀዋል። የቪኦኤ ጋዜጠኛ ማርት ቫን ደር ዎልፍ ጥቅምት 18፣ 2009 ባጠናቀረው ሪፖርት እንደዘገበው ጌታቸው እንዲህ ብሏል “እኛ ለመከተል የምንሞክረው የምርጫ ህጉ ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ ነው” “ይሄ መንግስት ድንገት ህጉን ለውጦ፣ በተለወጠው ህግም ምክንያት ምርጫ (አዲስ) የመጥራት ቅንጣትም ፍላጎት የለውም። እኛ እዚህ ያለነው ለዘለቄታው ነው።” ጌታቸውም ሆነ አለቆቹ የህወሓት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች ያልተገነዘቡት ወይንም መገንዘብ ያልፈለጉት ጉዳይ፣ የህዝቡ ምሬት አሁን በደረሰበት ደረጃ ፣ አዲስ ሃገራዊ ምርጫ ማካሄድ ህዝቡ ሊቀበለው የሚችለው ትንሹ አስታጋሽ እርምጃ እንደሆነ ነው። ይሄም የህዝብ ጥያቄ የህወሓት/ኢህአዴግ ቁንጮዎች በሚመፃደቁበት ህገ መንግስት ህጋዊ ድጋፍ እንዳለው አንቀጽ 54 ቁጥር 7 በደነገገው መሰረት “ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሰረት ከምክር ቤት አባልነት ይወገዳል” በማለት ግልጽ ያደርገዋል። ህዝብ ደግሞ በማያሻማ መንገድ የምክር ቤቱ አባላት ላይም ሆነ በመንግስት ላይ ምንም አይነት አመኔታ እንደሌለው ባለፉት አስራ አንድ ወራት ባካሄደው ትግሉ አረጋግጧል፣ ህዝባዊ ጥያቄውም አጥጋቢ መልስ እስኪያገኝ ድረስ ትግሉን ከመቀጠል ውጭ አማራጭ የለውም የበሰበሰ አይፀዳም! ፓርላማው ይበተን! ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ ይቋቋም! ሃገራዊ ምርጫ አሁኑኑ ይካሄድ! * ይሀን አጭር ጽሁፍ እያጠናቀርኩ እያለሁ የህዝብን ተቃውሞ ያስታግስልኛል ብሎ በማሰብ ጠቅላይ ምኒስትሩ አምና የሾማቸውን ሹመኛ ምኒስትሮች በውዞና አንዳንዶችንም ሸኝቶ አዲስ ካቢኔ ሰይሟል። ህወሃት እንደ ርስተ ጉልት ይዞት የነበረውን የውጭ ጉዳይ ምኒስቴር ለሌላ ማስተላለፉና በባለጌ አፉ ብዙ ሰው ያስቆጣ የነበረውን ጌታቸው ረዳን ማንሳቱ ጥሩ ቢሆንም ፣ሹም ሽሩ ፈጦ ላለው የህዝብ ጥያቄ በጭራሽ መልስ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ ያለአንዳች ተጨባጭ ማስረጃም ሆነ መረጃ ለእስር የዳረጋቸውን ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ቢፈታ እንደበለጠ በጎ እርምጃ መውሰድ ይቻል ነበር። በመሰረቱ ግን አሁን ሀገራችንን ከገባችበት አጣብቂኝ ማውጣት የሚቻለውና ህዝብ መንግስት ላይ ያለውን የተሟጠጠ ተስፋ በመጠኑም ቢሆን ሊያድስ የሚችለው፣ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ አቋቁሞ አሁኑኑ ሃገራዊ ምርጫ በማካሄድ አመኔታ እሚያሳድርባቸውን ሰዎች መምረጥ ሲችል ብቻ ነው።
(አበጋዝ ወንድሙ)

No comments:

Post a Comment

wanted officials