አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሂዩማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ይፋ ባደረጋቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ጋር በማንኛውም ስፍራ በአካል በመገኛኘት ለመወያየት እንደሚፈልግ አርብ ገለጠ። ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያቀርባቸውን ሪፖርቶችን ተከትሎ የቀድሞ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኢስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰፊ ምላሽን በመስጠት ተፈጽሟል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና ሂውማን ራይትስ ዎች በኢትዮጵያ ይፈጸማሉ በማለት ለህዝቡ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ትክክለኛ እንደሆኑና በባለሙያዎች ምርመራ የተካሄደባቸው እንደሆኑ አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለመንግስት በጻፈው ግልፅ ደብዳቤ ሲያካሄዳቸው በነበሩ ጥናቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ ተወካዮች ጋር በማንኛውም ስፍራ በአካል ተገናኝቶ መወያየት እንደሚፈልግ በደብዳቤው አስፍሯል።
በተቋሙ የአውሮፓ ህብረት ዳይሬክተር የሆኑት ሎቴ ለይችት ድርጅታቸው ቃለመጠይቅን ያደረገላቸው ግለሰቦችና ተቋማት ማንነት ለደህንነታቸው ሲል ይፋ ማድረግ ባይጠበቅበትም፣ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለጥያቄ የማይቀርቡ እንደሆኑ ገልጿል።
ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው ሂውማን ራይትስ ዎች አመልክቷል።
በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሃገሪቱ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማባባስ ስጋት መፍጠሩን ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጽ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ድርጁት የሚያወጣቸው ሪፖርቶች በሃገሪቱ በአካል ባለመገኘትና በትክክለኛ መንገድ ያልተካሄዱ ናቸው ሲል ማሳሰቢያን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሰሞኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ለተሾሙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በጻፈው ደብዳቤ መንግስት ተወካዮችን አዘጋጅቶ በጉዳዩ ዙሪያ ምክክር እንዲካሄድ ጥያቄውን አቅርቧል።
ተቋሙ ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ድረስ ከመንግስት በኩል ምላሽ እንዳልተሰጠው ታውቋል።
No comments:
Post a Comment