ኢሳት (ህዳር 8 ፥ 2009)
ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የከፋ ቁጥጥርና አፈናን ከሚያደርጉ ስድስት የአለም ሃገራት መካከል አንዷ ሆና መፈረጇን በጉዳዩ ዙሪያ ጥናትን ያካሄደ ያካሄደ አንድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ገለጠ።
መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገውና ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው ፍሪደም ሃውስ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ አፈናን የሚያደርጉ ሃገራት በመገናኛ ልውውጥ ላይ እንቅፋት መፍጠራቸውን አስታውቋል።
በአለማችን ካሉ ሃገራት መካከል ቻይና፣ ሶሪያ፣ ኢራን፣ ኢትዮጵያ፣ ኡዝቤኪስታን፣ እና ኩባ በቴክኖሎጂው ላይ መጠነ ሰፊ አፈናን ይፈጽማሉ ተብለው በግንባር ቀደምትነት የተቀመጡ ሲሆን፣ በአለማችን ካሉ ህዝቦች መካከል ከሁለት ሶስተኛ እጅ የሚልቀውን አፈናን በሚፈጽሙት ሃገራት እንደሚኖሩ ድርጅቱ አመልክቷል።
በቅርቡ መቀመጫውን በጣሊያን ያደረገ አንድ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የኢትዮጵያ መንግስት የስለላ ተግባር ለመፈጸም የሚያግዙ ቁሳቁሶችን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር በማፍሰስ ሲገዛ መቆየቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
በኢንተርኔት አገልግሎት እና አጠቃቀም ዙሪያ ጥናቱን ይፋ ያደረገው ፍሪደም ሃውስ በፈረንጆቹ 2015 አ ም የቴኖሎጂው ነጻነት ቁጥጥር የበዛበት መሆኑን አክሎ መንግስታት የማህበራዊ ድረገጾች ላይ የሚያደርጉት አፈና ተጠናክሮ መቀጠሉን በሪፖርቱ አስፍሯል።
አገልግሎቱን በከፋ ሁኔታ ይቆጣጠራሉ ተብለው ከተቀመጡት ስድስት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፈው አመት የኢንተርኔት አጠቃቀም ህግ ተግባራዊ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
በዚሁ አዋጅ መሰረት የኢንተርኔት አገልግሎትን በመጠቀም አመጽ ቀስቃሽ የሚባሉ መልዕክቶችንና አስተያየቶችን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ ያወጡ ግለሰቦች እስከ አምስት አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተደንግጓል።
ይሁንና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው ይኸው አዋጅ የመረጃ ልውውጥን ለማፈን የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ በመግለጽ ድርጊቱን ሲኮንኑ ቆይተዋል።
ፍሪደም ሃውስ ጥናንቱን ካካሄደባቸው 65 ሃገራት መካከል ከግማሽ የሚበልጡት የኢንተርኔት አገልግሎት በአሳሳቢ ደረጃ የሚገኝባቸው ሲሆን፣ በዩንጋንዳ፣ ባንግላዴሽና ካምቦዲያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀሙ ማሽቆልቆል ማስመዝገቡ ተገልጿል።
በቴክኖሎጂው አገልግሎት ላይ የከፋ ቁጥጥርን ያደርጋሉ ተብለው ከተቀመጡት ስድስት ሃገራት በተጨማሪ ሩሲያ ወደ ተመሳሳይ ድርጊት እየተጓዘች መሆኑ ስጋትን አሳድሯል ሲሉ የጥናት ሃላፊ አድሪያን ሻህባዝ (Adrian Shahbaz) ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ኢስቶኒያ፣ አይስላንድ፣ እና ካናዳ በአለማችን የኢንተርኔት አገልግሎትን ለተጠቃሚዎች በጣም ነጻ በሆነ መንገድ በማቅረብ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፣ አሜሪካ የግለሰቦችን ነጻነት በመጠበቅ የአራተኛ ደረጃን ይዛለች።
በአለም ከሚኖሩ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በቻይና ህንድና አሜሪካ እንደሚኖሩም ታውቋል።
በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ አለም አቀፍ ተቋማትና ኢምባሲዎች በአገልግሎት ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጥያቄን ቢያቀርቡም መንግስት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ እልባት እስኪያገኝ ድረስ እገዳው እንደሚቀጥል ገልጿል።
በተለይ በእጅ ስልክ ላይ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን፣ በመደበኛው መንገድ ተጠቃሚ የሆኑ ደንበኞችንም ተመሳሳይ ቅሬታን እያቀረቡ ይገኛል።
No comments:
Post a Comment