Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, November 28, 2016

የባለሥልጣናቱን ኪስ ነፍስ የሚዘራበት የኢትዮጵያ የስኳር ምርትና ፍላጎት


የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ስኳር የጫኑ 101 የከባድ ጭነት መኪናዎች አዋሽ ፍተሻ ጣቢያ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ እየተጉላሉ ነው ሲል አገር በዝምታ ተውጣ በትዝብት የምትከታተለውን የስኳር ወሬ ወደ ፊት አምጥቶታል።

ዜናው በማከልም “ዘጠኝ የደረቅ ትራንስፖርት ማኅበራት ተሽከርካሪዎችም ወደ ሀገር ውስጥ ምርቱን በማመላለስ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ 101 ተሽከርካሪዎች አዋሽ አርባን እንዳያልፉ መከልከላቸውን የኢትዮጵያ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ለኤፍኤም አዲስ 97.1 ባቀረቡት ቅሬታ ተናግረዋል። በተናጠል ከ430 እስከ 450 ኩንታል የጫኑትን ተሽከርካሪዎች ባሉበት እንዲቆሙ ያዘዘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተሽከርካሪዎቹ አዋሽ አርባን እንዳያልፉ የተደረጉት መጫን ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ ስለጫኑ ነው ብሏል።” በማለት የስኳሩን ጉዳይ ወደ ጎን በማለት የትራንስፖርት ችግሩ ላይ በማተኮር ዘግቧል።

በአገራችን የስኳር ምርጥ እጥረትና ችግር በአጭር ጊዜ እፈታለሁ ብሎ ለዓመታት ሲለፍፍ የከረመው መንግሥት ለዚህ አይነት ችግሮች ምላሽ ያለው እንደሆነ በማለት ኢብኮ ጋዜጠኞቹን ሊልክባቸው አልደፈረም፣ አይደፍርምም።

ባለፍው ዓመት 88 ሚሊየን ብር የት እንደደረሰ አጣሁ ያለው የስኳር ኮርፖሬሽን ለሕዝብ ፍላጎት የሚሆን አንዳችም ተግባር ሳይፈጽም ባዶ ወረቀት በፓርላማ አንብቦልን በነጻ የተሰናበተ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ዳይሬክተርና የዚሁ ፕሮጄክት ዋና ተዋናይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሀዬም ኮርፖሬሽኑን ጥለው ሹልክ ብለው እንዲወጡ ተደርጓል።

በየጊዜው የስኳር እጥረት የሚያሰቃየው የአገራችን ገበያ ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት ያን ያህል ቀላል ሆኖ አልተገኘም። የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን መረጃ እንደሚያሳየው የአገሪቱ የስኳር ምርት ፍላጎት ከምርት መጠን ጋር በፍጹም የማይጣጣምና፤ ይህም የፍላጎት መጠን በየዓመቱ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመሄድ ላይ መሆኑን ያሳያል።

ለምሳሌ እ.ኤ.አ. 2010 የስኳር ፍጆታ 500000 የነበረ ሲሆን፣ የምርት መጠኑ ደግሞ 290934 ብቻ ነበር። ይህም ፍጆታው ከምርት መጠኑ ጋር ፈጽሞ ያልተመጣጠነ እንደነበር ያሳያል። ይህንንም ክፍተት አገሪቱ እስከ 150000 ሜትሪክ ቶን ስኳር ከውጭ በማስገባት የአገሪቱን ገበያ ለማረጋጋት ተሞክሯል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ይህን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታትና ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የስኳር አምራች በመሆን የውጭ ንግዱን እመራለሁ በማለት ቁጥራቸው ወደ 10 የሚጠጉ የስኳር ፋብሪካዎችን እገነባለሁ ብሎ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፤ አንዳቸውም ግንባታ ጨረሰው ወደ ሥራ አለመግባታቸው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። እናም ዛሬም የአገሪቱ የስኳር ምርት ቀድሞ በነበሩት ሦስቱ የስኳር ፋብሪካዎች ጫንቃ ላይ እንደወደቀ ቀጥሏል።

በተለይ ደግሞ ይህንኑ ኃላፊነት በበላይነት ሲመሩ የነበሩት አቦይ ጸሀዬ ሥልጣናቸውን በጡረታ ሳቢያ መልቀቃቸው እጅጉን አነጋጋሪ ሆኗል። “የኮርፖሬሽኑን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ዕቅድ ከምን አድርሰውት ነው?” ከሚል ጥያቄ ጋር።

ይሁንና “መንግሥትስ ይህንን የገባውን ቃል አክብሮ መች ነው እነዚህ ፋብሪካዎች ለፍጻሜ ደርሰው የገበያውን ብርሃን ለማየት የሚበቁት? በዚህ ሰበብስ የሚበጀተው የሕዝብ ገንዘብ ማነው ሀይ የሚለው?” የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳነጋገሩ ይቆያሉ።

በአሁን ወቅት በሥራ ላይ ያሉት ሦስቱ የስኳር ፋብሪካዎች
ተ.ቁ የፋብሪካው ስም ያለበት አካባቢ ስፋት የተመሰረተበት አ.ም የማምረት አቅም
1 ወንጂ/ሸዋ ወንጂ 7050 ሄክታር 1947 80000 ቶን
2 መተሀራ መተሀራ 9919 ሄክታር 1961 115000ቶን
3 ፊንጫ ምስራቅ ወለጋ 6800 ሄክታር 1990 8500 ቶን


ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ (እ.ኤ.አ. 2012)

No comments:

Post a Comment

wanted officials