Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, November 13, 2016

ሪፕሪቭ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ መግለጫ አወጣ



ኢሳት (ጥቅምት 25 ፥ 2009)
የብሪታኒያ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ “ለህይወቴ” ስጋት አድሮብኛል ሲሉ መግለጻቸውን ይፋ እንዳደረጉ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ የሚከታተለው የሃገሪቱ የሰብዓዊ መግብት ተሟጋች ተቋም ገለጠ።
ሪፕሪቭ የተሰኘው ይኸው ተቋም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ባለፈው ሳምንት ያቀረቡት ስጋት ለቤተሰቦቻቸው በባለስልጣናት በኩል እንዲደርሳቸው መደረጉን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል የተባለው እስር ቤት ውስጥ ሁከት ተፈጥቶ እንደነበር ያስታወቁት የብሪታኒያ ባለስልጣናት ድርጊቱን ተከትሎ አቶ አንዳርጋቸው ለህይወታቸው ፍራቻ አድሮብኛል ሲሉ መግለጻቸውን ይፋ አድርገዋል።
የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ከነሃሴ ወር ጀምሮ አቶ አንዳርጋቸው ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻለ ረቡዕ ማስታወቁን ሪፕሪቭ የተሰኘ ተቋም በመግለጫው አስፍሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ሰኔ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ህጋዊ ምክር በሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል ሲል ማረጋገጫን ቢሰጥም እስከአሁን ድረስ የተወሰደ ዕርምጃ አለመኖሩ ታውቋል።
የአቶ አንዳርጋቸው የደህንነት ሁኔታ መነጋገሪያ እየሆነ መምጣቱን ያመለከተው የብሪታኒያው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሳምንታት ያህል ጉዳዩን ማረጋገጥ አለመቻሉን ስጋት እንደፈጠረበት አክሎ አመልክቷል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ይገኙበታል በተባለው እስር ቤት ሁከት ተፈጥሯል ቢባልም፣ በድርጊቱ ዙሪያ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።
ከአንድ ወር በፊት በቂሊንጦ ዕስር ቤት ተፈጥሯል የተባለን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ከእስር ቤቱ ለማምለጥ ሞክረዋል የተባሉ ከ200 በላይ እስረኞች መገደላቸው ይታወሳል።
የብሪታኒያ ባለስልጣናት በእስር ቤት ተፈጥሯል ያሉት ሁከት ከዚህ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።
በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑት ማያ ፍእ የብሪታኒያ ባለስልጣናት ከነሃሴ ወር ጀምሮ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳዩን አለማወቃቸው “አስደንጋጭ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አቶ አንዳርጋቸው ለህይወቱ ፍርሃት አድሮበት ይገኛል ሲሉ የገለጹት ሃላፊዋ፣ የብሪታኒያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን ለማድረግ ምን እንደሚጠቡቁ ግልፅ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ኮሚሽን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከእስር የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥያቄን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
አቶ አንዳርጋቸው በአሁኑ ወቅት ይጎበኙታል የተባለውን የደህንነት ሁኔታ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም።

No comments:

Post a Comment

wanted officials