*የአቅም ማነስ፣ አለመታዘዝና ችኩልነት በምክንያትነት ተጠቅሷል
*በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ላይ ያሳዩት ጣልቃ ገብነት ብዙዎችን አስቆጥቷል
*ለበጀት ዓመቱ ያቀረቡት የ13 ሚ. ብር ዕቅድ ጥያቄ አሥነስቶ ነበር
*በጎንደር እና በጎጃም ተቃውሞ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለው ነበር
*በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ላይ ያሳዩት ጣልቃ ገብነት ብዙዎችን አስቆጥቷል
*ለበጀት ዓመቱ ያቀረቡት የ13 ሚ. ብር ዕቅድ ጥያቄ አሥነስቶ ነበር
*በጎንደር እና በጎጃም ተቃውሞ፣ ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለው ነበር
ዛሬ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ ከፓትርያርኩ በተጻፈ ደብዳቤ፣ አባ ሠረቀ ብርሃን በእጃቸው የሚገኘውን ንብረት፣ ለልዩ ጽ/ቤቱ ሠራተኛ መጋቤ ሠናያት አሰፋ ሥዩም አስረክበው ቢሮውን እንዲለቁ መታዘዛቸው ታውቋል፡፡
አባ ሠረቀ ብርሃን፣ በተመደቡ በወራት ጊዜ ውስጥ ከሓላፊነታቸው የተነሡበት ምክንያት፣ በጽ/ቤቱ ሥራዎችና የአሠራር ግንኙነቶች የታየባቸው የአቅም ማነስ፣ አለመታዘዝና የታወቀው ችኩልነታቸው እንደኾነ ተገልጧል፡፡
የጽ/ቤቱን ሓላፊነት ከቀድሞው ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከተረከቡበት ካለፈው ዓመት ሐምሌ 12 ጀምሮ፣ ከሦስት ወራት በላይ ቢቆጠሩም፣ በተለይም የፓትርያርኩን ቃለ ምዕዳንና ቃለ በረከት የማሰናዳት ሥራው፣ በቀድሞው ልዩ ጸሐፊና በኮሚቴ እየተዘጋጁ መቀጠላቸው የአባ ሠረቀ የአቅም ክፍተት በጉልሕ የተጋለጠበት እንደኾነ ተጠቅሷል፡፡
ከዚኽም ባሻገር፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱና በልዩ ልዩ መምሪያዎች ሓላፊነትና ተግባራት ላይ የሚፈጽሟቸው ጣልቃ ገብነቶች፣ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁና ከዋና ሓላፊዎች ጋር ለበርካታ ግጭትና ጭቅጭቅ ሲዳረጋቸው እንደቆየ ታውቋል፡፡
ለዚኽም፣ ለ2009 ዓ.ም. አቅርበውት የነበረውና ለልዩ ጽ/ቤቱ ባልተለመደ አኳኋን የጠየቁት የ13 ሚሊዮን ብር የወጪ በጀት በአስረጅነት ተጠቅሷል፡፡ ለወትሮው ከ1.5 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ በጀት ለሚጠየቅበት የጽ/ቤቱ ዕቅድ፤ በአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ የለውጥ እንቅስቃሴን በማበረታታት፣ በገዳማት ርዳታ፣ መንፈሳውያን ኮሌጆችን በማጠናከር፣ የወጣቶችን ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር በማበልጸግና በመሳሰሉት ሰበቦች የቀረቡት ተግባራት ዝርዝር፣ የልዩ ልዩ መመሪያዎችን፣ ድርጅቶችንና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን ሳይቀር የሚጋፋና የሚሻማ እንደነበር ተገልጧል፡፡
በወጪ ዝርዝሮቹም ያካተቷቸው፡- በ2.3 ሚሊዮን ብር ወጭ የኹለት ሞዴል ሃይ ሉክስ ፒክ አፕ መኪኖችና የአጃቢ ሞተርኬዶች እንዲኹም በ300 ሺሕ ብር ዘመናዊ የጥበቃ ቴክኖሎጂዎች(የሰርቬላንስ ካሜራዎችና መፈተሻዎች) ግዥም፤ ከብክነትና ለመንበረ ፓትርያርኩ ካላቸው አግባብነት አኳያ ከፍተኛ ጥያቄዎች የተነሣባቸው ነበሩ፡፡
“የሌሎችን አካላት የሥራ ድርሻ ወደ ራሱ አምጥቶ ነበር ያቀደው፤” ያሉ አንድ የመንበረ ፓትርያርኩ ሓላፊ፣ አባ ሠረቀ ብርሃን፣ ያለብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ዕውቅናና ፈቃድ፣ የመምሪያ ሓላፊዎችን ስብሰባ ጠርተው በዕቅዱ ላይ እስከማወያየትና ጫና እስከ መፍጠር ደርሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ይኸው የአባ ሠረቀ ብርሃን ዓምባገነናዊ ጣልቃ ገብነት፣ አቅምን አውቆና ዐቅዶ በመሥራት ረገድ ቀደም ብሎም በዋና ሓላፊነት በተመደቡባቸው መምሪያዎች የነበረባቸውን ውስንነት በጉልሕ ያረጋገጠና፣ ከሌሎች ጋር ተግባብቶ ሓላፊነትን ለመወጣትም ያለባቸውን ከፍ ያለ ጠባዕያዊ ድክመት ያጋለጠ ኹነኛ ምስክር ኾኖባቸዋል፡፡
ተግባብቶ የመሥራት ችግራቸው፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ዕለታዊ መርሐ ግብሮች፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለማቀድ መሰናክል ከመኾን አልፎ፣ ልዩ ጽ/ቤቱን ለከባድ የሕዝብ ግንኙነት ኪሳራ እንደዳረገውም ምንጮች አስረድተዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አራተኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ፣ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲፈጸም ፓትርያርኩ ያልተገኙት፣ አባ ሠረቀ ከመጋቤ ካህናቱ ጋር በፈጠሩት ጭቅጭቅ መርሐ ግብሩ ባለመያዙና ፓትርያርኩ እንዲያውቁት ባለመደረጋቸው ነበር፡፡ የሌሎች አብያተ እምነት መሪዎች ሲገኙ የፓትርያርኩ መቅረት ባስነሣው ጥያቄ፣ ግንኙነታቸው ለረጅም ጊዜ ሻክሮ ቆይቷል፡፡
አባ ሠረቀ በሓላፊነታቸው አጋጣሚ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን፣ ፖለቲካዊ ልባስ በመስጠትና ከመንግሥት ጋር በማገናኘትም ይታወቃሉ፡፡ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊነታቸው ወቅት፣ ከአሠራርም በላይ ሃይማኖታዊ አቋማቸውንና በኑፋቄ ከሚጠረጠሩ አካላት ያላቸውን ግንኙነት መነሻ በማድረግ የተጠየቁባቸውንና እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የደረሰ ጉዳያቸውን፣ “ቤተ መንግሥቱ እና ቤተ ክህነቱ ከማያውቋቸው ሥውራን ኃይሎች ጋር በሐቀኝነት በመታገሌ ነው” በሚል ማኅበሩን እንደምን በአክራሪነት ወንጅለው ጉዳዩ የፖሊቲካ ሽፋን እንደሰጡት የሚታወስ ነው፡፡
በአኹኑ የልዩ ጸሐፊነታቸው የወራት ዕድሜ እንኳ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ፣ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ ብፁዓን አባቶችና በርካታ የመምሪያ ሓላፊዎች በተገኙበት ያካሔደውን 9ኛ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ያልተፈቀደና ሕገ ወጥ ነው በሚል፣ በልዩ ጽ/ቤቱ ስምና በበላይ ሓላፊው ሊቀ ጳጳስ ቲተርና ፊርማ ባወጡት ደብዳቤ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የጠቅላላ አገልግሎት ሓላፊና የአዳራሹን ቁልፍ ያዥ አስጠንቀቅዋል፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ መልእክት ያስተላለፉ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን የመምሪያ ሓላፊዎች ስም በዝርዝር ለይተው በመያዝ ለማሸማቀቅ ሞክረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም፣ አዳራሹን ለማንኛውም ስብሰባው መጠቀም እንደማይችል ገልጸው እንዳይፈቀድለት ጠቅላይ ጽ/ቤቱን አዝዘዋል፡፡
ከዚኽም በላይ፣ ብፁዓን አባቶችን እያገኙ፣ “ማኅበረ ቅዱሳን አኹን አብቅቶለታል፤ መንግሥት አኹን ዐውቆታል፤ የጎንደሩና የጎጃሙ ብጥብጥ ዋነኛ መሪዎች የማእከላቱ አመራሮችና አባላት እንደኾኑ መንግሥት መረጃ አለው፤ ተጠንቀቁ፤ ግንኙታችኹን አቁሙ!” በማለት ማስፈራራታቸው ተረጋግጧል፡፡ እንደ ልዩ ጽ/ቤቱ ሓላፊ መጠን፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የቤተ ክርስቲያንን ሚና ለማስረዳት የሚሰጡት መግለጫም ብዙ የተተቸበት ነው፡፡
ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ ለኤጲስ ቆጶስነት ከተጠቆሙት አንዱ ቢኾኑም፣ በነገረ ሃይማኖት በተለይም በነገረ ማርያም የተጠየቁበትና በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሠረት ምላሽ ያልሰጡበት አቋማቸው በማስረጃ ተደግፎ ጥቆማቸው በአስመራጭ ኮሚቴው ውድቅ ተደርጓል፡፡ እርሳቸው ግን፣ ማኅበረ ቅዱሳንንና የኮሚቴውን ብፁዓን አባቶች ከመክሠሥ አልፈው፣ የልዩ ጽ/ቤት ሓላፊነታቸውን በመጠቀምና በውጫዊ ኃይል ግፊት ጭምር፣ ግልጽና ስልታዊ ጫናዎች ለማሳደርና ለሢመቱ ለመታጨት የቻሉትን ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
በፓትርያርኩ የሚሰጧቸውን የልዩ ጽቤት ሥራዎች፣ “ጥቆማዬን ይደግፉልኛል” ከሚሏቸው ወገኖች አኳያ እየለዩ በአፈጻጸም ያሳዩት ተፃራሪነትም፣ በመጨረሻ ከፓትርያርኩ ጭምር አጋጭቷቸው የልዩ ጸሐፊነት ሥራቸውን አሳጥቷቸዋል፡- በአቅም ማነስ፣ በአለመታዘዝና በችኩልነት ተወግደዋል!!
ምንጭ:- ሃራ ተዋህዶ
No comments:
Post a Comment