(ዘ-ሐበሻ) ከመሳሪያ ትግል ወደ ሰላማዊ ትግል በማምራት ከኦነግ ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባርነት የተቀየረው የአቶ ሌንጮ ለታ ኦዴፍ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አርበኞች ግንቦት 7 ጋር በጋራ ለመስራትና ወደ ጥምረትም ለማምራት ንግግር ላይ እንዳሉ የዘ-ሐበሻ ምንጮች አስታወቁ::
የዘ-ሐበሻ ምንጮች እንዳሉት የሌንጮ ለታ ኦዴፍ አሁንም ሃገር ቤት ገብቶ መታገልን እንደአማራጭ የያዘ ሲሆን ሁለገብ ትግልን ከሚያራምደው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር ለመስራትና ለመጣመር የወሰነው በተለይ በሃገር ቤት ያለው የፖለቲካ ምህዳር የባሰ እየጠበበ ከመጣ በኋላ ነው ተብሏል::
በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ንግግሩ የተጀመረው ቆየት ብሎ ነው ያሉት የዘ-ሐበሻ ምንጮች አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በመጪው ኦገስት ወር ላይ ጥምረታቸውን ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ብለዋል::
አቶ ሌንጮ ለታ ትግሎ ሃገር ቤት መግባት አለበት ብለው ወስነው ኢትዮጵያ ሄደው ከኤርፖርት መንግስት እንደመለሳቸው ይታወሳል:: ኢትዮጵያ በሄዱበት ወቅትም ጀነራል ሳሞራና የደህንነቱ ሚንስተር አቶ ጌታቸው አሰፋ አቶ ሌንጮን ለማሰር ሞክረው ሌላ ሃይል ወደ መጡበት ይመለሱ በሚል ወደ መጡበት እንዳስመለሳቸው የዘ-ሐበሻ ምንጮች ይናገራሉ
http://www.zehabesha.com/amharic/archives/62669
No comments:
Post a Comment