Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 6, 2016

ሰበር ዜና – የፓትርያርኩ ልዩ ጸሐፊ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ከልዩ ጽ/ቤቱ ተወገዱ!



  • ምንም ዓይነት ምደባ አልተሰጣቸውም
  • ምደባቸውን በውጭ ኾነው ይጠባበቃሉ
  • “ቦታ የለኝም”/ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ/
  • ቀጣዩ ልዩ ጸሐፊ ከዋና ሥራ አስኪያጁ ጋር በመመካከር ይመደባል፤ ተብሏል
*               *               *
 Pat Abune Mathias and Nibure'Ed Elias Abreha
በፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የልዩ ጸሐፊነት ሥልጣናቸው ተገን፣ የሙስና ሰንሰለት ዘርግተው ሕገ ወጥ ሀብት በማካበትና በክፉ ምክራቸው ለበርካታ የውስጥ አለመግባባት መንሥኤ የነበሩት የመዝባሪዎች አለቃ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ከሓላፊነታቸው ተወገዱ!!
ልዩ ጸሐፊው፣ በእጃቸው የሚገኘውን ንብረት፣ ዛሬ፣ ሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም.፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ቀሲስ፣ አባ ኪዳነ ማርያም ደስታ አስረክበው፣ ልዩ ጽ/ቤቱን እንዲለቁ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከቅዱስነታቸው በተላለፈ ትእዛዝ መሠረት ነው፣ ዛሬ ከቀትር በኋላ ከሓላፊነታቸው ከልዩ ጽ/ቤት ሓላፊነታቸው የተወገዱት፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ፣ ከሓላፊነታቸው ከተወገዱ በኋላ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ከሚገኙት ድርጅቶች አልያም መምሪያዎች በአንዱ፣ በዋና ሓላፊነት ሊመደቡ እንደሚችሉ ቀደም ብሎ ቢዘገብም፣ ምንም ዓይነት ምደባ እንዳልተሰጣቸውና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቦታ ተገኝቶላቸው እስኪመደቡ ድረስ እንዲጠባበቁ በፓትርያርኩ ከተጻፈላቸው የማሰናበቻ ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ የንቡረ እዱን ተለዋጭ ምደባ አስመልክቶ ከፓትርያርኩ እንደተጠየቁና፣ “ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ውጭ ካልኾነ፤ ቦታ የለኝም፤” ማለታቸውን የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡
ንቡረ እዱ፣ በአስተሳሰባቸው ይኹን በተግባራቸው ያሉበት ብልሹ ተክለ ሰብእና፣ ከመንበረ ፓትርያርኩም ኾነ ከልዩ ጽ/ቤቱ ደረጃ እና ክብር ጋር በመሠረቱ የማይጣጣምና የቅዱስነታቸውም ልዩ ረዳት ሊኾኑ እንደማይገባ በመጥቀስ ከቦታው እንዲርቁ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልአተ ጉባኤ ደረጃ፤ ቋሚ ሲኖዶሱም በመደበኛ ስብሰባዎቹ እንዲኹም፣ ብፁዓን አባቶችና የፓትርያርኩ የቅርብ ወዳጆች እንደ ግለሰብ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ሲመክሩና ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡
በግንቦቱ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ልዩ ጸሐፊው ሳይገባቸው ከያዙት ቦታ በአጭር ጊዜ እንዲነሡ፣ ምልአተ ጉባኤው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ጥብቅ ማሳሰቢያ እንደሰጣቸውና ቅዱስነታቸውም፣ ይህንኑ እንደሚፈጽሙ ማረጋገጣቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ 
“አንዴ፣ ምልአተ ጉባኤው ሳያልቅ አያንሡኝ፤ ሌላ ጊዜ ትምህርቴን እስክጨርስ ይታገሡኝ” የሚለው የንቡረ እዱ ተማኅፅኖ፣ ፓትርያርኩን እስከ አኹን ድረስ እንዳዘገያቸው ቢገለጽም፤ ዋናው መንሥኤ፣ በቦታው የሚተካና የፓትርያርኩ ምርጫ የኾነ ሰው አለመገኘቱ ነው፤ ይላሉ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች፡፡
ልዩ ጸሐፊው፣ ልዩ ጽ/ቤቱን ዛሬ ከቀትር በኋላ ለአቡነ ቀሲሱ ሲያስረክቡ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያው ዋና ሓላፊ መጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም፣ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ዋና ሓላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል እና የውጭ ግንኙነት መምሪያ ዋና ሓላፊ መልአከ ሰላም ‘አባ’ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ በእማኝነት ተገኝተዋል፤ ተብሏል፡፡
የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅና በአሜሪካ ስለ ጤና አገልግሎት አስተዳደር በሚያማክር ብሔራዊ ኩባንያ ውስጥ በፕሬዝዳንትነት የሚሠሩ የፓትርያርኩ የቅርብ ወዳጅ፣ ዶ/ር ሙሴ ሐረገ ወይን ቦታውን እንደሚይዙና ጥሪም እንደተላለፈላቸው ሲገለጽ ቢቆይም፣ ፓትርያርኩ ለኤጲስ ቆጶስነት ከጠቆሟቸው ቆሞሳት መካከል አንዱ የኾኑት፣ አወዛጋቢው ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ሊተኩ እንደሚችሉ ከወዲኹ ተገምቷል፡፡
በሌላ በኩል፣ የግንቦቱ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ፣ የልዩ ጽ/ቤቱ አወቃቀር፣ ተግባርና ሓላፊነት በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረቱን ይዞ፤ በአስፈላጊው የሰው ኃይል ተደራጅቶ በሊቀ ጳጳስ እንዲመራ የወሰነው ተግባራዊ እስኪኾን፤ ቀጣዩ ልዩ ጸሐፊ፣ ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ ዲዮስቆሮስ ጋር በመመካከር እንደሚመደብ ነው፣ እየተገለጸ የሚገኘው፡፡
Nibure'Ed Elias Abreha Mesfin
በአቋቋም የመዘምርነት ሞያ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ መስፍን፣ ከአንድ ዓመት በፊት ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በማታው መርሐ ግብር በሥነ መለኰት በዲፕሎማ፣ ዘንድሮ ደግሞ በዲግሪ 
“በከፍተኛ ማዕርግ” ተመርቀዋል፤ ከአልፋ ዩኒቨርስቲበማኔጅመንት በርቀት የወሰዱት ሌላ ዲፕሎማ እንዳላቸውም ተገልጧል፡፡
ንቡረ እዱ፣ በልዩ ጸሐፊነት ልዩ ጽ/ቤቱን ከተቆጣጠሩበት ካለፈው ዓመት ወዲኽ ያለው ጊዜ አጭር ቢኾንም፣ የሚሰጡትን ክፉ ምክርና የሚያረቋቸውን ደብዳቤዎች ተከትሎ፣ ፓትርያርኩ ባራምዷቸው ሕግንና ምክረ አበውን የሚጥሱ አቋሞች፤ የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ስምና ዝና የሚጎዱ በርካታ ውዝግቦች ተፈጥረዋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችንና የቋሚ ሲኖዶስ መመሪያዎችን በቸልታ እየተላለፉ፣ የጠቅላይ ጽ/ቤቱንና የአህጉረ ስብከትን ሥልጣንና ተግባር እየተሻሙ፣ ከብፁዓን አባቶችና ሌሎች አስፈጻሚ አካላት ጋር አባታዊ እና የሥራ ዝምድናን የሚያሻክሩ ከፍተኛ አለመግባባቶች ተከሥተዋል፡፡ 
ፓትርያርኩ ራሳቸው፣ በየመድረኩ የሚናገሩላቸው፤ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ የሚያስቀምጡ፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍኑ፣በበጎ ፈቃድ የተደከመባቸው የተቋማዊ ለውጥ ተስፋዎችና ጅምሮች በከንቱ መክነዋል፡፡
Addis Ababa Sunday Schools at the Holy Synod Opening Prayer
ይህም በውጤቱ በሚፈጥረው የብዙኃን ተቃውሞና ግፊት፣ ፓትርያርኩ ንቡረ እዱን መልሰው የወቀሱባቸው ጥቂት አጋጣሚዎች የነበሩ ቢኾንም፣ በአብዛኛው ግን፣ በፓትርያርኩ ዘንድ የማይተኩ አለኝታ ተደርገው የታዩበትና፤ ከጥቂት ባለሥልጣናት ጋርም ልዩ ቅርበት የፈጠሩበት አጋጣሚ እንደነበር ነው የሚታመነው፡፡
አዲስ አበባ የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ከመኾኑም ጋር ተያይዞ፣ ንቡረ እዱ ቀደም ሲል በሥራ አስኪያጅነት ሲሠሩ በዘረጉትና በልዩ ጸሐፊነታቸው ተገን ባጠናከሩት የምዝበራ ሰንሰለት፤ ከጉዳይ ማስፈጸም፣ ከአለቆችና ሠራተኞች ዕድገትና ዝውውር ተቀማጫቸውን አድልበዋል፤ በቀጣይም፣ በከተማው የተለያዩ ይዞታዎቻቸው ለከፍተኛ ‘ኢንቨስትመንት’ መዘጋጀታቸው ይነገራል፡፡
በቤተሰባዊነት የሚዛመዷቸውን የወቅቱን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ በማስመደብ፤ እንዲኹም፣ በቅርቡ፣ የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በሌሉበት፣ ከአስተዳደር ጉባኤው ዕውቅና ውጭ አልቆ በመጣው ከደርዘን በሚልቁ የአድባራት አለቆችና ጸሐፊዎች ዝውውርና ምደባ፣ፓትርያርኩን በመወትወት ጭምር የነበራቸው ወሳኝ ሚናና ያተረፉበት ኹኔታ፤ ‘የኢንቨስትመንት’ ድልባቸውን ያጠናከሩበት መሰናበቻ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በሀገረ ስብከቱ፣ በሥራ አስኪያጅነት በሠሩበት 2003 ዓ.ም.፣ በምዝበራ ሰንሰለቱ ያሉ የጥቅም አጋሮቻቸው፣  በልማት ጉብኝት ስም አጥንተው በሚያመቻቹላቸው የዘረፋ ስልት፣ በየአድባራቱ በሚዘዋወሩበት ወቅት፣ “የኮቴ” የተሰኘና በእያንዳንዱ ከ25ሺሕ ያላነሰ ብር የሚቀበሉበትአማሳኝነት/አንቃዥነት፣ በንቡረ እዱ የተጀመረ ውርስ እንደኾነ፣ ከእርሳቸውም በኋላ የቀጠለና ዛሬም ድረስ የሚነገር እውነታ ነው፡፡
ከመናፍስት ጋር በተያያዙ ክፉ ልማዶች ጭምር ስማቸው የሚነሣው የቀድሞው መሪጌታ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ንቡረ እድ ከተባሉበት የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ካቴድራል በሕዝብ እንዲባረሩ ያደረጋቸው ይኸው የምዝበራ አመላቸው ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ አድባራት ራሱን ችሎ በሙዳየ ምጽዋት በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሠራው የካቴድራሉ ሙዝየም ግንባታ ውል፣ በተፈጸመበት ኹኔታም ክፉኛ መወቀሳቸው አልቀረም፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ ለአጭር ጊዜም ቢኾን፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በዲንነት፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት መንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነትም ሠርተዋል፡፡
Nibure'Ed Elias Abreha00
ብልጡ መለኛ ንቡረ እድ ኤልያስ፣ ከፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የመወገዳቸው ጉዳይ፣ ለረጅም ጊዜ በተለያየ መልክ ሲገለጽ ቢቆይም፣ ዛሬ ተጨባጭ እስኪኾን ድረስ፣ ብዙዎችን፣ “ካላየን አናምንም” አሰኝቷቸዋል፤ አይነኬ እና ምትሃዊ አድርገው የሚያዩዋቸውም አልጠፉም፡፡
ንቡረ እዱ፣ በተማሪ ቤት ሥልጥንናቸውን ያሳዩበትን የአቋቋም ሞያ ይዘው፣ ወደ አዲስ አበባ በ1980ዎቹ አጋማሽ ሲገቡ፣ አገልግሎታቸውን የጀመሩት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመዘምርነት ነበር፡፡ ከልዩ ጽ/ቤቱ መወገዳቸው እውን ኾኖ ዛሬ ከሓላፊነታቸው ሲነሡ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ቦታ ይፈለግላቸው ቢባልም፣ ትክክለኛ ምደባቸው ከመዋቅራዊ ሓላፊነት ውጭ በተወሰነ ቦታ እንዲኾን ብዙዎች ይሻሉ፤ መቼም ለተጠያቂነት ሥርዓቱ አላደለንምና!!

ሐራ ዘተዋሕዶ

No comments:

Post a Comment

wanted officials