Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, July 16, 2016

የጎንደር ህዝብ ህዝባዊ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታወቀ



የጎንደር ህዝብ ህዝባዊ ትግሉን እንደሚቀጥል አስታወቀ
ሐምሌ ፯ ( ሰባት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች የኮሚቴ አባላት መታሰራቸውን ተከትሎ በጎንደር ከተማ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ፣ በደባርቅ የተደገመ ሲሆን፣ የዳባት ወረዳ ወጣቶችም ወደ ደባርቅ በመሄድ ህዝባዊ አመጽ ጀምረዋል። የወልቃይት ጠገዴን ህዝባዊ ጥያቄ ሲመሩ በመጨረሻም መሳሪያቸውን አንግበው ሲፋለሙ የተገደሉት ባለሃብቱ አቶ ሲሳይ ታከለ በጎንደር ከተማ ደማቅ የሆነ የጀግና የቀብር ስነስርዓት ከተደረገላቸው በሁዋላ ፣ የአመጹ አስተባባሪዎች ፣ በእስር ላይ የሚገኙት የኮሚቴ አባላት ካልተፈቱ እንዲሁም የማንነት ጥያቄያቸው ካልተመለሰ አፈሙዛቸውን ወደ ክልሉ መንግስት እንደሚያዞሩ አስጠንቅቀዋል። በአደራ መልክ የተሰጡት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ለትግራይ ደህንነቶች ተላልፈው የሚሰጡ ከሆነም፣ ትግሉ የመረረ ይሆናል ሲሉ ማስጠንቀቂያ ልከዋል።
ህዝባዊ አመጹ ወደ ደባርቅ ተሸጋግሮ የደባት ወጣቶች ወደ ደባርቅ በማምራት ትግሉን የተቀላቀሉ ሲሆን፡ የህወሃት ንብረት የሆኑ ከ10 በላይ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶችን፣ መኖሪያ ቤቶችንና እንዲሁም 3 ተሽከርካሪዎችን በእሳት አጋይተዋል። የከተማው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ለ25 አመታት የተጫነብን የህወሃት አገዛዝ በቃ በማለት መፈክሮችን ሲያሰማ የዋለ ሲሆን፣ ከሰአት በሁዋላ ደግሞ የህወሃት የመንገድ ስራ ኩባንያ የሆነውን አኬር የተባለውን ድርጅት ለማቃጠል ህዝቡ መንቀሳቀሱንና የፌደራል ፖሊስ አባላትም ከወጣቶች ጋር መጋፈጣቸውን የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
አብዛኛው የታጠቀው የሚሊሺያ አባል ከህዝቡ ጎን በመቆም የህወሃት አገዛዝ ይብቃን እያለ ነው። ብአዴን በአፋጣኝ ውሳኔውን ካላሳወቀ ጥቃቱ በብአዴን ላይ እንደሚዞርም እያስጠነቀቀ ነው። በደባርቅ፣ ዳባትና አጎራባች ቀበሌዎች የሚገኙ የመንግስት ሹሞች እየሸሹ ሲሆን፣ ወደ ትግራይ የሚወስደውም መንገድም ተዘግቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials