Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, July 18, 2016

የአሜሪካ ሴናተሮች አገራቸው ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ እንድትመረምር ጠየቁ






የኢትዮጵያ መንግስት አክቲቪስቱን አንዳርጋቸው ጽጌን በማፈን በህገ ወጥ መንገድ በማሰሩና በአገሩ ውስጥ በሚፈጽማቸው ጥሰቶች የተነሳ የአሜሪካ ሴናተሮች ኮሚቴ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ እንድትመረምር ለማድረግ ጥሪ ለማቅረብ የሚያስችለውን ረቂቅ ለማጽደቅ የመነሻ ይሁንታን ከሰኔቱ ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡
ረቂቁ ‹‹ድጋፍ ለሰብዓዊ መብት መከበርና መልካም አስተዳደርን በኢትዮጵያ ማበረታታት››የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በሰኔቱ የህግ አውጪዎች ስብሰባ ወቅት የመጀመሪያውን ደረጃ ለማለፍ የሚያስችለውን ማረጋገጫ በውጪ ግኑኝነት ኮሚቴ ውስጥ ከሚገኙ ሴናተሮች ማግኘቱ ተጠቅሷል፡፡
በረቂቁ የሰፈረው ጽሁፍ የኢትዮጵያ መንግስት በእስር ላይ የሚገኙ ተቃዋሚዎቹን፣አክቲቪስቶችንና ጋዜጠኞችን እንዲለቅና መንግስትን የሚተቹ ሰዎችን ለማሰር እየተጠቀመበት የሚገኝን ህግ እንዲያርምና የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ለኢትዮጵያ በመሰጠት ላይ የሚገኘውን የደህንነት ድጋፍ እንዲገመግሙ ይጠይቃል ፡፡
ረቂቁ የቀረበው ከአሜሪካ ጋር ግኑኝነት ያለውና በእስር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚና አክቲቪስት የአንዳርጋቸው ጽጌ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑ በተነገረበት ወቅት ነው፡፡ባለቤቱና ልጆቹ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው እንግሊዛዊው አንዳርጋቸው በወርሃ ሰኔ 2006 ከየመን አየር መንገድ ታፍኖ ወደኢትዮጵያ ከተወሰደ በኋላ በ2002 በሌለበት የተላለፈበት የሞት ፍርድ ተግባራዊ ሊደረግበት እንደሚችል ተሰግቷል፡፡አንዳርጋቸው ላይ የሞት ፍርድ የተላለፈበትን ሂደት የተከታተሉት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በጊዜው ውሳኔው ፖለቲካዊ ብቀላና ችሎቱም መሰረታዊ የሚባሉ የህግ ሂደቶችን ያልተከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአንዳርጋቸው ባለቤት ይኖሩባት የነበረችው ሜሪላንድ ከተማ ሴናተር የሆኑት ቤን ካርዲን ረቂቁን በዋናነት ለሰኔቱ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡ሴናተሩ ቤን ካርዲን የአንዳርጋቸው ጉዳይ በኢትዮጵያ የመንግስት ተቃዋሚዎችን እንደሚወክል ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ዝነኛ የሆኑት አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ በ1998 ለአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት ንግግር አድርገው ነበር፡፡ለሴኔቱ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ‹‹በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ የሚገኘው የአፈና መጠን በአገሪቱ የጭለማ ወቅት ተደርጎ ይቆጠር በነበረው በወታደራዊው አገዛዝ ይፈጸም ከነበረው ልቋል››በማለት ተናግረው ነበር፡፡
አንዳርጋቸው ከታፈኑበት ቅጽበት ጀምሮ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቤተሰቦቻቸው ጨምሮ በማንም እንዳይጎበኙ አድርገዋል፡፡በምርመራ ላይ እንደነበሩ የሚያሳይ ቪዲዮም በብሄራዊው ቴሌቭዥን አማካኝነት ለእይታ አቅርበዋል፡፡ቶርቸር በኢትዮጵያ ወህኒ ቤቶች የተለመደ በመሆኑም አንዳርጋቸውም ቶርቸር ሳይፈጸምባቸው እንዳልቀረ ስጋቶች አሉ፡፡
ባለፈው ዓመት የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ታሪካዊ ጉብኝት በማድረግ ወደኢትዮጵያ ባመሩበት ወቅት የአገሪቱን ገዢ ፓርቲ የተቃዋሚዎቹን ድምጾች በማፈኑና ህጋዊነትን ባለመከተሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር፡፡የአንዳርጋቸው ጽጌን ቤተሰቦች በመደገፍ ላይ የሚገኘው አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሪፕራይቭ ለኦባማ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ ኦባማ የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ሲገናኙ የአንዳርጋቸውን ጉዳይ እንዲያነሱባቸው ተማጽንኦ የነበረ ቢሆንም ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡
በሪፕራይቭ የሞት ቅጣትን ከመላው አለም ለማስቀረት ንቅናቄ በማድረግ ላይ የሚገኘውን ቡድን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ማያ ፎ ‹‹ላለፉት አመታት የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን፣ጦማርያንንና ተቃዋሚ አክቲቪስቶችን ለማፈን ያለተቃውሞ የሄደበትን የአፈና መንገድ ሴናተሮቹ ማውገዛቸው ትክክል ነው፡፡በመንግስት ጥቃት ከደረሰባቸው አንዱ አንዳርጋቸው ነው፡፡ አንዳርጋቸው በዛ ያሉ ጉዳቶች ደርሰውበታል፡፡ከአፈና ጀምሮ ቶርቸር ተፈጽሞበታል፡፡በሌለበት የሞት ፍርድ የተላለፈበትን አንዳርጋቸውን አሜሪካዊያኑ ቤተሰቦቹ አጠገባቸው ሊያገኙት በእጅጉ ይናፍቃሉ፡፡የኦባማ አስተዳደር በኢትዮጵያ የህግ የበላይነትንና ዴሞክራሲን ለማሻሻል ቆራጥ ከሆነም ዋይት ሐውስ ከሴኔቱ የሚቀርብለትን የማንቂያ ደወል በአስቸኳይ በማድመጥ እንደ አንዳርጋቸው ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲለቀቁ መስራት ይኖርበታል››ብለዋል፡፡
የወሬው ምንጭ ሪፕራይቭ

No comments:

Post a Comment

wanted officials