ሁለት የጉራጌ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን አቶ አሊ ሁሴንና ዶክተር ያእቆብ ኃይለ ማርያም ይባላሉ። ሁለቱ ደግ ሰዎች ግፍና በደል የህይወቱ አካል ለሆነው ድምጽ አልባ አማራ የእድሜ አጋሮቻቸው የሆኑት የአማራ ገበሬ ልጆች ካደረጉት በላይ በመጮህ ስለ አማራ መገደል፣ መፈናቀል፣ መሰደድ፣ ስለተፈጽመበት የዘር ማጥፋትና እልቂት አጋጣሚው በፈቀደው ቦታና ሰዓት ሁሉ ሳይታክቱ የአማራ ሙሉ ድምጽ በመሆን ድንቅ ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
አቶ አሊ ሁሴን ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ናቸው። የኢህአፓ ታጋይ ሳሉ «አማራ ነህ» ተብለው ሞቃዲሾ በስደት ላይ ሳሉ የአማራን ግፍና በደል ተቀብለዋል። አቶ አሊ ይህንን ግፍና በደል ዶክመንተሪ ሰርተው፤ መጽሀፍ ጽፈውና በተለያዩ ቦታዎች ንግግር በማድረግ ለአለም ሁሉ አሳውቀዋል።
እነ መለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ ሞቃድሾ ጽህፈት ቤት ከፍተው ኢትዮጵያን ሲያጠቁ በሲያድ ባሬዋ ሶማሊያ እስር ቤቶች ውስጥ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይና አማርኛ አስተርጓሚ ሆነውም ይሰሩ ነበር። አቶ አሊም ከደርግ እስር ሸሽተው ወደ ሶማሊያ ተሰደው ሚቃዲሾ እስር ቤት በገቡበት ወቅት በነመለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ ጥቆማ «አማራ ነህ» ተብለው በተለየ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተደርገው የተፈጸመባቸውን ግፍ፤ በሌሎች «አማራ ናቸው» በተባሉ ላይ የተካሄደባቸውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ፤ በሴት እህቶቻችን ላይ የደረሰውን ከአእምሮ በላይ የሆነ ዘግናኝ ጭካኔ ዝርዝር በሰሩት ዶክመንታሪና በመጽሀፋቸው ነግረውናል። በተለያየ ጊዜ በሰጡት ቃለ መጠይቅም አቶ አሊ ሶማሊያ ውስጥ «ሸለምቦት» በተባለ ቦታ «የአማራ» ተብሎ በተከለለው እስር ቤት ውስጥ ስለተፈጸመው ግፍ ዛሬም ድረስ ህመሙ እየተሰማቸው ይናገራሉ።
እኒህ የአማራ ባለውለታ ላለፉት ሰላሳ በላይ አመታት ስለ አማራ ሲጮሁ ኖረዋል። ከነቤተሰቦቻቸው በአማራ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል ተናግረው አይደክሙም! «ኢትዮጵያዊ ነኝ» በማለታቸው «አማራ ነህ» ተብለው የደረሰባቸው ግፍና በደል የአማራ ድምጽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል! በየተገኙበት መድረክ ሁሉ አጥንታቸው ድረስ የሚሰማቸውን የአማራ ግፍና በደል ከፍ አድርገው ይናገራሉ! በደልና ግፍ የህይወቱ ገጽታ የሆነው አማራ ይነሳ ዘንድም ከአመታት በፊት እንዲህ ሲሉ ተቀኝተዋል፤
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ነበረ ተረቱ፣
ምነዋ ዘንድሮ ተወጊው ሲረሳ ወጊ አለመርሳቱ፤
ከዚያም አልፎ ተርፎ የተወጊው ጉዳይ የከበደው ነገር፣
በደሉን ረስቶ የወጋውን ጩቤ ልሶ ስሞ ማደር!
ከዚህ በተጨማሪ አቶ አሊ ሐረር ውስጥ አማራ ከነነፍሱ በተጣለበት የማይሞላ ገደል ስም “እንቁፍቱ” የሚልና “ፈርዶበት አማራ!” በሚል ርዕስ አስደማሚ ግጥሞች ጽፈዋል። አቶ አሊ ዛሬም ስለ አማራ ግፍና በደል መናገራቸውን አላቆሙም። በሚኖሩበት ካናዳም የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች አንድነት ኮሚቴ የሚል ማህበር መስርተው የሕሊና እስረኞች ድምጽ ናቸው።
ሌላኛው የጉራጌ ተወላጅ የአማራ ድምጽ አዲስ አበባ የሚኖሩት ታዋቂው የዓለም አቀፍ የህግ ባለሙያ ዶክተር ያእቆብ ኃይለ ማሪያም ናቸው። ዶክተር ያቆብ ኃይለማርያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሩዋንዳ የተካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለማስቻል አቋቁሞ በነበረው አለም አቀፍ ፍርድ ቤት ላይ በዋና አቃቤ ህግነት ያገለገሉት የአለም አቀፍ ህግ ምሁር፤ ለአገራችን ችግሮች ብዙ የመፍትሄ ሃሳቦች ያቀረቡና አሰብ የኢትዮጵያ ወደብ መሆን እንደሚገባት አለም አቀፍ ሕግን በማጣቀስ «አሰብ የማን ናት» በሚል ርዕስ መጽሃፉ አሰናድተው በአሰብ ዙሪያ ያለውን ብዢታ ያጠሩ አገር ወዳድ የህግ ሊቅ ናቸው።
No comments:
Post a Comment