Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, July 12, 2016

“ፍምን እፍ ብትላት ትነዳለች ፣ትፍም ብትልባት ትጠፋለች፣ሁለቱም ሁሉ ከአንድ አፍ ይወጣሉ፤ ” መጽኃፈ ሲራክ ም/ ፳¥ ቁ Ú፪ ይገረም አለሙ






ፍም አስፈላጊም አላስፈላጊም የሚሆንበት ወቅትና ምክንያት ይኖራል፣ ይህን ለይቶና ተገንዝቦ እፍንም ትፍንም እንደአግባቡ መጠቀም ውጤታማ ያደርጋል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚቻለው እንቅስቃሴው ግላዊም ይሁን ድርጅታዊ መነሻውን ያወቀ፣ መሄጃ መንገዱን የለየ፣ መድረሻ ግቡን በግልጽ ያስቀመጠና ለግል ሥልጣንና ጥቅም በማሰብ ሳይሆን ሀገርንና ህዝብን በማስቀደም ላይ የተመሰረተና በስሜት ሳይሆን በእውነት በግብታዊነት ሳይሆን በእቅድና በስልት የሚከናወን ሲሆን ነው፡፡

ነገር ግን በትንሹ የሁለቱን አብዮቶች ዘመን (ህዝባዊ አብዮትና አብዮታዊ ዴሞክራሲ)ትግሎች ብናይ በመጀመሪያው አብዮት ወቅት ሁሉም ለሶሻሊዝም እውን መሆን ነው የምንታገለው ይሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ዓላማቸውም ሆነ ግባቸው ከሚሉትና ከሚጽፉት በስተጀርባ የተደበቀው የግል ሥልጣን ሆነና ፍሙን መቼ፤ እንዴትና በምን ሁኔታ እፍ ብለው ማቀጣጠል ወይንም ትፍ ብለው ማጥፋት እንዳለባቸው ባለመገንዘብ ወይንም የየግል ፍልጎታቸው ይህን ለማየት እድል ነፍጎአቸው ሊጠቀሙበት በሚገባው ፍም ራሳቸው ተቃጥለው ጠፉ፡፡ ወቅት ጠብቀው አጋጣሚን ተጠቅመው ሁሉም በአንድ ትንፋሻቸውን አስተባብረው ፍሙን እፍ በማለት የጋራ ጠላታችን በሚሉት ደርግ ላይ እሳቱን ማቀጣጠል ቢችሉ አላስፈላጊ በሆነ ግዜም እንትፍ ብለውበት ሊያጠፉት አሌም ሊያበርዱት ቢሞክሩ የደረሰው የሰው አልቂት የንብረት መውደምና የሀገር ክስረት ባልተከሰተ ነበር፡፡ ነገር ግን ባልተጠና ባልታቀደ ግብታዊ ሁኔታ አንዱ ፍሙን ሊያቀጣጥል እፍ ሲል ሌላው ደግሞ በዛው ቅጽበት ትፍ እያለ ሊያጠፋ ሲጣጣር ደርግ ምቹ ሁኔታ አገኘና እፍም ትፍም ባዮችን ተራ በተራ በላቸው፡፡ የሚያሳዝነው የዚሁ ድርጊት ፈጻሚዎች ከዚህ መማር አለመቻላቸውና ይህንኑ ራሳቸውን ለሽንፈት ሀገሪቱን ለውድቀት የዳረገ ተግባር እስከ ዛሬ የቀጠሉበት መሆኑ ነው፡፡

በሁለተኛው አብዮት ማለትም በዘመነ ወያኔ በተቃውሞው ጎራ የታየውና አሁንም የሚታየው ተመሳሳይ ነው፡፡ በተቃውሞ ጎራ ተሰልፈናል የሚሉት በሀገራዊና በጎሳ የተከፋፈሉ ቢሆኑም ሁሉም ለዴሞክራሲ ነው የምንታገለው፣ ህዝብን የሥልጣኑ ባለቤት ማድረግ ነው ግባችን ወያኔን ለማስወገድ ነው ትግላችን ይላሉ፡፡ ሀያ አምስት አመት ቀላል አይደለምና ብዙዎችን ከተግባራቸው እንደመዘናቸው ይህ የሚናገሩትና የሚጽፉት ማስመሰያ ሆኖ ዋናው ዓላማና ግባቸው ራስን ለቤተ መንግሥት ማብቃት ነው፡፡ በእውነቱ ለዚህ የሚበቃ አቅም ኖሯቸው መንገዱንም ይዘውት ቢሆን መመኘታቸው ባልከፋ፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ ታጋይ ነን በምርጫ መንግሥት እንሆናለን የሚሉት ብዙ ናቸው፣ አንዳቸውም ግን 100 ዕጩ እንኳን ማቅረብ ሳይችሉ ነው እናሸንፋለን የሚሉት፡፡በዚሁ አቅማቸው ደግሞ ርስ በርስ ይፎካከራሉ ይጠላፋሉ፡፡

ምርጫን በቅዱስ መጽፍ የተገለጸውን ፍም አድርገን ብንመስለው ፍሙ ተቀጣጥሎ ወያኔን ለሽንፈት እነርሱን ለቤተ መንግሥት ሊያበቃቸው የሚችለው ትንፋሻቸውን አሰባስበው በአንድ ላይ እፍ ብለው ሊያቀጣጥሉት ቢችሉ ነበር፡፡ ሲሆን አላየንም፣ እንደ አያያዛቸው መቼም የሚሆን አይመስልም፡፡ በተቃራኒው የሚታየው አንዱ እንደምንም ተውተርትሮ ፍሙን ለማቀጣጠል እፍ ማለት ከጀመረ ሌላው ተሯሯጦ በአለው አቅም እትፍ ብሎ ለማጥፋት ሲንደፋደፍ ነው፡፡

ወያኔን መጣል በሚገባው ቋንቋ ነው ብለው የነገሩንና ጠመንጃ ማንሳታቸውን ያወጁትም ድርጅቶች ብዙ ናቸው፡ አንዳንዶቹ የወያኔን የሥልጣን ዘመን አስቆጥረዋል፡፡በቆይታቸው አንዳቸውም ለቤተ መንግሥት የሚያበቃ አይደለም መኖራቸውን የሚያሳይ ተግባር አላከናወኑም፡፡ ይህ ማለትም በተናጠል አቅም የላቸውም ማለት ነው፡፡ ተባበሩ ካልሆነም ተከባበሩ የሚለው የማህበረሰቡ ጩኸትም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ታዲያ አንዳንዶቹ አቅማቸውን አውቀው ሁኔታውን ገምግመው ለተባበሩ ጥያቄውም ዋጋ ሰጥተው ትብብር በመፍጠር ፍሙን በጋራ እፍ ብለው ለማቀጣጠል ወደ ሚያስችል ደረጃ ሲያመሩ በአንጻሩ ሌሎች እትፍ ብሎ ለማጥፋት ይዘጋጃሉ፡፡ ወያኔን ለማስወገድ ነው የምንታገለው እያሉ ፍሙ በወያኔ ላይ እንዲቀጣጠል የትንፋሽ እገዛ ማድረጉ ቢቀር እትፍ ብሎ ለማጥፋት መሽቀዳደሙ እንቆቅልሽ ነው፡፡

ሌላው አንቆቅልሽ እፍም ትፍም የሚሉበትን ወቅትና ምክንያት አጋጣሚውንም አለመለየት ነው፡፡ እፍ መባል በሚገባው ግዜ እንትፍ እያሉ የህዝቡን ትግሉን ያዳክማሉ፣ ሞራል ይገድላሉ ተስፋ ያስቆርጣሉ፡፡ በተቃራኒው አንትፍ መባል ባለበት ሰአት ፍሙን በወጉ አቀጣጥለው ላያቀጣጥሉት እፍ እያሉ ዜጎችን ለአልተገባ መስዋዕትነት ይዳርጋሉ፤ለወያኔ የፕሮፓጋንዳም ለኃይል ርምጃም መንገድ ይሰጣሉ፡፡ ይሄ በየዘመናቱ የታና የሥልጣን ጥም ለመማር እድል የማይሰጥ ሆኖ ዛሬም እየተፈጸመ ያለ እኩይ ድርጊት ነው፡፡

ወያኔ ግን ፍሙን እፍ ብሎ የሚያቀጣጥልበትንም ሆነ ትፍ ብሎ ማጥፋት ያለበትን ግዜና ምክንያት በውል ስለሚያውቅ ሀያ አምስት አመት በወንበሩ ለመዝለቅ አስችሎታል፡፡ ሌሎቹን ትተን በቅርቡ የተፈጸመውን ለአብነት እናንሳ፡፡ ወያኔዎች የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የሚሉትን ከማክበራቸው ቀደም ብሎ በቴሌቭዥናቸው ያሰራጩትና አንዳንድ ሰዎች በኢሰፓ ርዕዮት ዓለም መምሪያ የተዘጋጀ የሚመስል በማለት የተሳለቁበት ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚሰብክ ዶክመንተሪ፤ከዛም ቀጥሎ በብሄረሰቦች ቀን ክብረ በአል ላይ ያለወትሮው ኢትጵያዊነት የሚል ቃል አብዝቶ የተሰማበት የጠቅላይ ምኒስትር ኃለማሪያም ደሳለኝ ንግግር የተቀጣጠለውን የህዝብ ፍም አንትፍ በማለት ለማጥፋት ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ መሆኑ አጠራጣሪም አነጋጋሪም አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል የጎሰኝነት ፍሙ ከእነርሱ እጅ የወጣ አስምስለው በሌሎች አንዲቀጣጠል እፍ ከማለትም አልፎ ሲያራግቡት አናያለን እንሰማለን፡፡ በአንድ በኩል በአንድ ብሄር ስም ስድስት ሰባት ድርጅቶች ተፈጥረው እነርሱም ርስ በርሳቸው ስምምነት እንዳይኖራቸው ብሎም በኢትዮጵያዊነት ላይ እንዲዘምቱ መደረጉ አንዴ እየተቀጣጠለ የሚለበልበውን ሌላ ግዜ እየተዳፈነ በእትፍ አይደለም በምንም በምንም ተሞክሮ አልጠፋ ያለውን የኢትዮጵያዊነት ፍም ለማጥፋት የሚደረግ ስራ መሆኑ ያልተከሰተለት ኢትዮጵያዊ ካለ የሀገሩን ጉዳይ ምን አገባኝ ብሎ የተወ ብቻ መሆን አለበት፡፡

እፍም ሆነ እንትፍ ከአንድ ሰው ሲወጣ ደካማ ነው፡፡ ብዛቱ በጨመረ ቁጥር ግን የማቀጣጠሉም ሆነ የማጥፋት አቅሙ ይጨምራል፡፡ስለሆነም አውቃችሁ በድፍረት ወይንም ሳታውቁ በስህተት በመታለልም ሆነ በመደለል እፍታችሁንም ሆነ ትፍታችሁን ባልተገባ ቦታ ግዜና መንገድ እያዋላችሁ ያላችሁ ወገኖች ያደረጋችሁትን እያደረጋችሁ ያላችሁትንና ድርጊታችሁ ያስገኘውን ውጤት ወደ ፊትም ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለአፍታ ቆም ብላችሁ መርምሩ፡፡

አሁን ያለው አሰላለፍ ሁለት ነው፤የወያኔ ሥርዓት እንዲቀጥል ፣ አለያም ኢትዮጵያ ከወያኔ አገዛዝ ተላቃ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመሆን እንድትበቃ መታገል፡፡ ከራስ በላይ ማሰብ ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸውና ትናንት በሥልጣን ጥም እየናወዙ ወጣቱን ግን ስለ ዴሞክራሲ እየሰበኩ ያስጨረሱት የማይቆጫቸውና የህሊና እዳ ያልሆነባቸው እንዲሁም እነርሱን መሰል አዲስ በቀሎች የሚቃዡበትን ሥልጣን የሚያገኙ በመሰላቸው ቦታ ሁሉ እዛም እዚህም ሲረግጡ አይተናል፡፡ወያኔም ማቀጣጠል የሚፈልገውን በቅርብ ሆኖ እፍ ለማለት ማጥፋት ካልሆነም ማቀዝቀዝ የሚፈልገውም ላይ አንትፍ ማለት እንዲያስችለው በሁለተኛው አሰላለፍ ውስጥ የሚያሰርጋቸው ከዚህ አልፎም የተቀዋሚ ካባ አልብሶ የሚያሰማራቸው ስለመኖራቸው የአደባባይ ማስጢር ነው፡፡

ብዙኃኑ ግን አሰላለፉን በግልጽ መለየት ከቻለ ሁሉም ነገር ንጥር ብሎ ባይለይ እነኳን እፍም ሆነ እንትፍ በተቃውሞው ጎራ በትክክልና በተባበረ ሁኔታ ስራ ላይ እንዲውል በአንጻሩ በወያኔ በኩል የሚፈጸመ ውጤታማ እንዳይሆን ማድረግ ይቻላል፡መጽሀፉ ከፍሬአቸው ታውቁአቸዋላችሁ እንደሚለው የህዝባዊ ትግሉን ፍም እፍ ብሎ ለማቀጣጠል ትንፋሽ የማያዋጡም ሆኑ ሌሎች ትንፋሻቸውን አስተባብረው ፍሙን ለማቀጣጠል እፍ ሲሉ እንደ አቅማቸው ለማጥፋት እንትፍ የሚሉ የፈለጉትን ምክንያት ቢደረድሩ ከነጻነት ትግሉ ጎራ አይደሉምና ከእነዚህ በግዜ መለየት ነው፡፡

ስለሆነም ሰዎችንም ሆነ ድርጅቶችን ከተግባራቸው በመለየት ፍሙን መቀጣጠል ሲያስፈልግ እፍታችንን፣ ማጥፋት በሚያስፈልግበት ወቅት ደግሞ ትፍታችንን በመለገስ እንተባበር በአንድ እንቁም፡፡ እፍ የሚሉ እየመሰሉ አንትፍ የሚሉ አንትፍ የሚሉ እየመሰሉ እፍ የሚሉ የነጻነት ትግሉ ከሚፈልገውና ከሚጠይቀው በታቃራኒ የሚፈጽሙ የበግ ለመድ ለብሰው በመካከላችን የተሰገሰጉ ተኩላዎችን እንለይ እንወቅ እንጠንቀቅ ፡፡ ቅዱስ መጽኃፍም ይላል፡፡

የሐዋርያው የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ ም/፫ ቁ»–Ú፩

ነገር ግን ሞኝነት ካለው ምርመራና ከትውልዶች ታሪክ ከክርክርም ስለ ሕግም ከሚሆን ጠብ ራቅ፣ የማይጠቀሙና ከንቱዎች ናቸውና ፣መለያየትን የሚያነሳ ሰው ጠማማ እንዲሆን በራሱም ላይ ፈርዶ ኃጢአትን እንዲያደርግ አውቀህ አንድ ግዜ ሁለት ግዜ ከገሰጽኸው በኋላ አንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ፤

No comments:

Post a Comment

wanted officials