Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, July 7, 2016

የሃይማኖት አባቶች ብታውቁበት ሀብታሙም የንስሐ ልጃችሁ ነበር | የጉዳያችን አጭር ማስታወሻ

  • የሃይማኖት አባቶች  ዛሬ ሀብታሙን ልጄ አደለም አላውቀውም ብለው መካዳቸው እንደ ጴጥሮስ መክዳት ያለ ግን  ዶሮ እስኪጮህ  ድረስ ብቻ  የሚቆይ መሆኑን አላውቁትም 
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ተመልሶ መምጣቱ እና እውነተኛ ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት በዓለም ላይ ምን አይነት ምልክት እንደሚታይ ያሳወቀበት የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 እና 25 አንዱ ነው። በእነኝህ የመፅሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ ሐሰተኛ ነቢያት እንደሚነሱ ከተቻላቸው የተመረጡትን ሁሉ እንደሚያስቱ ይገልፃል።
በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 25 ቁጥር 41 ላይ እንዲህ ይላል : –
«ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ? ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?» ይሉታል። እርሱምመልሶ በሕይወት ዘመናቸው ከእነርሱ ለሚያንሱት ያደረጉትን መልካም የቸርነትና ትህትናሥራ እንደዋጋ ቆጥሮላቸው «እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት» ማቴ 25፣41
የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ ፣በህወሓት እስር ቤት የማቀቀው ሀብታሙ፣ በአንድ ወቅት አቶ መለስ በብሩህ አእምሮው ያደነቁት እና እንደሚፈሩት ያሳበቀባቸው ሀብታሙ፣ የዛሬውን የአልጋ ላይ ተኝቶ በህመም የሚሰቃየው ሀብታሙን ተገብተን ከላይ የተፃፈውን ጥቅስ እንመልከተው።
የሃይማኖት አባቶች ልጆቻቸውን በዘር በአካባቢ ትውልድ፣ቤተ መንግስት ያለውን ሰው ፊት እየተመለከቱ በሽተኛ የሚጠይቁ መሆን አለበት? የሃይማኖት አባቶችን አድር ባይነት በየዘርፉ ጠግበነዋል። ይህንን አድርባይነት በዝምታ ሽንገላ እግዚአብሔርን መደለል ከተቻለ ጥሩ ነው።ኢየሱስ ክርስቶስ ለሀብታሙ ያደረጋችሁት ለእኔም አደረጋችሁት የለናል።ለሃይማኖት የፓርቲ እና የአመለካከት መለክያ እንደ መስፈርት ከተቀመጠ ይህንን ዓለም ማን ሊዳኛት ነው?
አድር ባይነትን በእጃቸው በያዙት መስቀል ሸፍነው ጌቶቻቸው አይዟችሁ እንዲሏቸው እና ሃቀኛ መስለው በመታየት የሃይማኖት አባቶች ዛሬ ሀብታሙን ገፍተውታል። ሀብታሙን ሄዶ ሆስፒታል መጠየቅም ሆነ ሕክምና ይፈቀደለት ብሎ መጠየቅ ከጮማው እና ከቀይ ወይን ብሎም ከምሽት ውስኪ ያጎድላል እና ማንም የሃይማኖት አባት ተብዬ ለሀብታሙ የሚጮሁትን ሁሉ አይሰሙም።ሀብታሙም የንስሐ ልጄ አይደለም ማለት ለጊዜው ከባለ ጊዜዎች ሙገሳ እና የጀግና መዳልያ ያሰጣልና የሃይማኖት አባቶች አይናቸውን ሳያሹ አላውቀውም ለማለት እየዳዳቸው ነው።
አሁን ያለንበት ዘመን መስሎ አዳሪ፣ለጥቅም እና ለይሉኝታ የገዛ ልጁን የሚገፋ የሃይማኖት አባት የሞላበት ነው።ከመንግስት ጋር የሚያጣላ የመሰለው ልጁ ነገ አገር ቤት ያለው ጥቅም ያሳንሳል አለፍ ሲል በዘመኑ ገዢዎች ፊት ያስነሳል እና ሀብታሙን መራቅ ብቸኛ አማራጭ ነው።ይህ ግን የሃብታሙን ክብር አይነካውም።ይልቁንም በእግዚአብሔር ዘንድ የበለጠ ክብር በሰው ዘንድም ሞገስን ከአምላኩ ይቀበልበታል።ለአመታት በጨበጡት መስቀል ለሕዝብ አንዳች ነገር ያልሰሩ የገበታ ላይ ወሬ አድማቂዎች የሃይማኖት አባት ተብዬዎች ግን አድር ባይነታቸው እንዳየለባቸው ፀሐይ ትጨልምባቸዋለች። ቢያውቁበትማ ኖሮ  ሀብታሙን መጠየቅ ሕክምና ይፈቀድለት ማለት ከማቴዎስ ወንጌል የክርስቶስ ቃል ጋር መስማማት መሆኑን በተረዱት እና በተጠቀሙበት ነበር።የእነርሱ መንደር ልጅ ያልሆነው ሀብታሙ ግን ዛሬ የእነርሱ ልጅ አይደለም።በሚስጥር የሚገናኙት  ከአራት ኪሎ ጌቶቻቸው ጋር ነው።በእነርሱ ቤት ይህንን ዓለም አያውቅም። የሃይማኖት አባቶች  ዛሬ ሀብታሙን ልጄ አደለም አላውቀውም ብለው መካዳቸው እንደ ጴጥሮስ መክዳት ያለ ግን  ዶሮ እስኪጮህ  ድረስ ብቻ መሆኑን አላውቁትም።ዶሮ ይጮሃል! አይዘገይም ማን ለወያኔ አድሮ ማንን እንዳሳደደ፣ማን ለሕዝብ ቆሞ ኢትዮጵያን እንዳላቆሰለ የሚለይበት ቀን አይዘገይም።
ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com
 Habtamy Ayalew

No comments:

Post a Comment

wanted officials