የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ በትኩረት እየተከታተሉት እንደሆነ ዴቪድ ካሜሩን ለእንግሊዝ ፓርላማ ገለጹ
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ መንግስታቸው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተከታተለ እንደሚገኝ ለሃገራቸው ፓርላማ ገልጹ።
የሃገሪቱ ፓርላማ ሰሞኑን በተለያዩ የብሪታኒያ አበይት ጉዳዮች ዙሪያ ልዩ ጉባዔን ባካሄደ ጊዜ ክሪስ ሎው የተባሉ የፓርላማ አባል ተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዴቪድ ካሜሩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ከማስፈታት ስለሚወስዷቸው እርምጃዎችን ጥያቄን አቅርበዋል።
በብሪታኒያው አለም አቀፍ ማሰራጫ ረቡዕ በቀጥታ ባስተላለፈው በዚሁ የፓርላማ ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ሃገራቸው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።
ሃገራቸው ዜጋዋ የሆኑትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ለመከታተል የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለሁለት አመት ያህል ጊዜ በእስር ላይ መቆየታቸውን ያወሱት የስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ ተውካይ የፓርላማ አባሉ ክሪስ ሎው ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡ ጊዜ የፓርላማ አባላት ያላቸውን ድጋፍ ሲገልፁ ታይተዋል።
መቀመጫቸውን በብሪታኒያ ያደረጉ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ችላ ብለዋል በማለት የተቃውሞ ዘመቻን ሲያከሄዱ መሰንበታቸው ይታወቃል።
ባለፈው ወር ወደ ኢትዮጵያ ይተጓዙት የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃመንድ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የህግ ምክር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው።
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ ምላሽን የሰጡት ዴቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሃላፊዎች ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።
የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን በመከታተል ላይ የሚገኘው የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሪፕሪቭ የብሪታኒያ መንግስት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰው ስምምነት አቶ አንዳርጋቸው ከእስር እንዲለቀቁ የሚያደርግ መሆን አለበት ሲል መግለጹ ይታወሳል።
መንግስት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በሌሉበት ቅጣት የተላለፈባቸው በመሆኑ የህግ አገልግሎት አያስፈልጋቸውም ሲል ከብሪታኒያ መንግስት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽን ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
No comments:
Post a Comment