Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, July 12, 2016

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ሰቆቃ፤ – በበ. ደ. ኮሬ፡ ቶሮንቶ፤ ካናዳ

Ethiopian-Airlines-Logo
እነሆ ከሁለት ወራት በፊት ቶሮንቶ ስገባ፤ በረጅሙ ነበር እፎይ ….. ብዬ የተነፈስኩት፡፡ ለረጅም ዘመን በሰቀንና በፍርሀት ውስት ስለኖርኩ፤ አሁንም ሙሉ በሙሉ ነጻነት ተስምቶኛል ብዬ ባላስብም፤ ለጊዜው ግን የተሰማኝ እፎይታ ነው፡፡ መንግስታችን በሚከተለው “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” አስተሳሰብ የፈጠረውን ድህነትና የትምህርት ዋጋ ማጣትን እንደ ልማት ከተጠቀሙ ድርጅቶች አንዱና ተቀዳሚው የራሱን ዜጎች ማክበር አቅቶት ስለ አህጉር የሚያወራው አየር መንገዳችን፤ ስርዐቱን ጠብቆ ባልተጠና መልኩ የሚከተለው የሰው ሀይል አስተዳደር ቢሮው፤ በየጊዜው የተማረውን እና ሀገር ተረካቢውን የሰው ሀይል እንደ ቤተ ሙከራ ግብዐት እየተጠቀመ፤ ዜጎችን በዕዳ ተብትቦ ዘመናዊ ባርነትን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡

ከእያንዳንዱ ስኬት በስተጀርባ የጠንካራ ሰራተኞች የሌት ተቀን ልፋት መነሳቱ አይቀሬ ነውና፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተልዕኮ መሳካት ከሚሳተፉት ውስጥ የጥገና ባለሞያዎች ሚና በከፍተኛ የሚጠቀስ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ክፍል ውስጥ የተለያየ ማንነትና ትምህርት ደረጃ ያላቸው ሰራተኞች የያዘው አየር መንገዳችን፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቀው የአቬሽን ሙያ ላይ ያሰማራቸው ዜጎቹን ለተከታታይ ስምንት የስራ ሰዐታት ዳቦና ሻይ እያበላ፤ አቅማቸውና የስራ ደረጃቸው ከሚፈቅደው በላይ ሰራ በማሰራት በጫና ምክንያት ለሚፈጠሩ ስህተቶች፤ የሀገር ንብረት ሆነ ብላችሁ ለማጥፋት ወይም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናችሁ በሚል ሰበብ፤ ማዕከላዊ አስገብቶ ከማስደብደብ፤ እስከ ቤተሰብ በታኙ እስር ማድረስ የተለመደ ተግባሩ እየሆነ መጥቷል፡፡ የስራ ቋንቋውን ወደትግርኛ የቀየረው የድርጅቱ ጥበቃ ክፍል ዋነኛ ግቡ ሰራተኛውን ማንገላታት ካደረገው ሰንበት ብሏል፣ ሰራተኛው ተስፋ ቆርጦ መባረሩን ወይም መታሰሩን እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ግቢው ውስጥ ፈገግታ የሚታየው ከላይ ያሉ ሰዎች ፎቶግራፍ ሲለጥፉ ብቻ እየሆነ መጥቷል፡፡

ለምሳሌ፤የLine maintenance ስራ፤ ከጠዋቱ 6 am – 2 pm ድረስ ይቆያል፡፡ ከላይ እንደጠየቅኩት፤ ይህን ያህል ሰዓት፤ ያለምንም ምግብ አቅርቦት (ሻይና ዳቦ) እንዲሁም በቂ እረፈት ይከናወናል፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይም ይሁን በሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ በሚያነሳ ሰራተኛ ላይ ማስፈራሪያና ሌላም እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከ promotion & training ማስተጓጎል፣ ተገቢውን ጥቅም መከልከል፣ ከ Europe & North America flight ላይ ማገድ በተጨማሪም የ security ክትትል እንዲደረግባቸው ማድረግ ናቸው፡፡ አሁን አሁን ምርጫ ጠፍቶ እንጂ፤ አስተዳደሩ፤ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ በራሪዎች ያንድ ብሄር ብቻ ተወላጆች ቢሆኑ ይወዱ ነበር፡፡

ከ January 1, 2016 ጀምሮ የሚተገበር የ maintenance ሰራተኞችን የዕድገት ደሞዝ እርከን ሰራተኛውን ሳያማክሩ መቀነስ እና ስብሰባ ጠርተው በዚህ ዙርያ ጥያቄ ለሚያነሳ ወገን ማስፈራሪያ መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ ካልፈለጋችሁ እናንት ጥላችሁ መሄድ ትችላላችሁ፤ እኛ ደግሞ ያስተማርንበትን እናስተፋችኋለን በማለት በሀላፊው አቶ መስፍን ማስፈራሪያና እና ንቀት ያዘለ መልዕክት መተላለፉ የዘወትር ቀለብ ነው፡፡

ሰራተኛውን ያለፍላጎቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ማሳተፍ ሌላው በደል ነው፡፡ ለምሳሌ የግንበት 20 በአል ማክበር እና የመለስ ሙት አመትን በግድ ሻማ እንዲያበሩ ሰራተኞችን ማስገደድ ጉልህ ምሳሌ ነው፡፡ ያለ ሰራተኛው ፍቃድ (ሰራተኛውን ሳያማክሩ) ከደሞዝ ላይ የተለያዩ መዎጮ መቁረጥ፣ ያለ ሰራተኛው ፈቃድ ወይም ተጨማሪ ክፍያ ስምምነቱ ከሚፈቅደው በላይ ማሰራት እና ጥያቄ የሚጠየቁ ሰራተኞችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መቅጣት የተለመደ ነው፡፡

ብሄርን መሰረት ያደረገ ውይይትም ትችትም አልወድም፡፡ ነገር ግን ይሄ ስርአት ያመጣብን አንድ ነገር ቢኖር፤ ብሄርን መሰረት ያደረገ ውይይትና ትችት ውስጥ እንድንገባ ማድረጉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግቢና በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ቦታዎች ለትግራይ ተወላጆች መስጠት ህግ እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ቢተዉንም መልካም ነበር፡፡ ከዚም አልፈው መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡናል እንጂ፡፡ የትግራይ ብሔር ተወላጅና የሕወሀት ደጋፊዎች በ እነ Yibrah Welderufael (የጂኔራሉ ልጅ) ፣ Kibrom (wide body hangar acting manager) እና በአቶ ዘላለም (base maintenance director) የተደራጀው ቡድን በግቢው ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችን ባጣመረ መልኩ ሰራተኛውን የመሰለልና ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ የማሰልቸት ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ረገድ እንደምሳሌዎች መጠቀስ ያለባቸው፤ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆነ ሰራተኛ ምንም አይነት ጥፋት ቢሰራ የመከላከል እና በእሱ ላይ ህጉን አክብረው የሚያስዳድሩትን አለቆች ግን ምክንያት ፈጥሮ እስከማባረር መድረሱን ነው፡፡ በግቢው ውስጥ የማን አለብኝነት እና የባለቤትነት ስሜት ማስረፅም አንዱ ጉልህ መጠቀስ ያለበት ምሳሌ ነው፡፡ ሶሻል ሚድያ ላይ ከሕወሀት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የተነሱአቸውን ፎቶግራፎች (Photographs) በተደጋጋሚ መልቀቅና አንድ አንድ ፖለቲካዊ መልእክቶችን ማስቀመጥ የመወደጃ መስፈርት ነው፡፡ ለመብታቸው ጥያቄ የሚያቀርቡ ሰራተኞችን ያለ ምክንያት የማንገላታትና ከSecurity ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አስመስለው ከስራ እስከ ማሰናበትም ሌላኛው ክፉ ድርጊት ነው፡፡

ከግቢው የ security ቡድን ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመሰራት ያሻቸውን ምክንያት እየፈለጉና እያስፈለጉ ሰራተኛውን ማንገላታት፤ በዝምድና እና በእውቅና መሿሿም እንዲሁም ለአለቆች የማጎብደድን ስርዓት ፈጥረው በሰራተኛው ዘንድ ጫና ማሳደር የተለመዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡ በአሁኑ ሰዐት Lome በሚገኘው hub director ሆኖ የተሾመው እና የቀድሞው የ line maintenance director አቶ ቅዱስ መልካሙ የ CEO (ተወልደ ገ/ማርያም) የባለቤቱ እህት ልጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የሴኩሪቲ አባላት ላይ ያለውን ወሳኙን እና የአመራሩን ቦታ በትግራይ ተወላጆች መሙላት፣ ከዚህ በፊት ቃሊቲ ወህኔ ቤት ይሰራ በነበረው በቅፅል ሰሙ “ወዲ ሻምበል” በሚባለው ግለሰብ የሚመራው የድርጅቱ ሴኩሪቲ ለፖለቲካው ጥቅም ሲባል ሰራተኛው ለይ በተለያ መልኩ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ አንዳንድ ግዜ ሰራተኛውን የሚያንገላቱበት ሰበብ ተራና የወረደ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የድርጅቱን ንብረት በማን አለብኝነት የሚጠቀሙት እኚሁ የሴኩሪቲ አባላት፤ ሌላውን ሰራተኛ የታሸገ ውሀ ለምን ጠጣህ፤ ኩኪስ በላህ፤ ብለው መታወቂያ ቀምቶ በሰዎች ፊት ከማንገላታትና ከማዋረድ፤ እስከ ደሞዝ ቅጣት ያደርሳሉ፡፡ ያም አልበቃ ካላቸው አለባበስህ አያምርም ወይም ፂምህን ለምን እንዲህ ተቆረጥክ በማለት ከስራ ቦታ እስከማስወጣት ደርሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሰራተኞች የሚኖሩበት ግፍ አያሌ ነው፡፡

ነፃ አውጭዎቻችን እንደ ኮንስትራክሽን ዘርፉ ዜግነትን በደረጃ ወረቀት ላይ ባያስቀምጡትም፤ መተግበሩ ላይ ግን ከራሳቸው አልፈው ለልጆቻቸው እያወረሱ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች በየቢሮዎችና በከተማ ውስጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መገንዘብ ከበድ ያለ አይመስልም፡፡ የዚሁ ደረጃ ተጠቃሚዎች በዚህ ድርጅት ውስጥ መንፀባረቅ ከጀመረ ጥቂት ጊዚያት ተቆጥረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል የአንድ መከለከያ ባለስልጣን ልጅ በአጭር ጊዜ የስራ ልምድ ግቢው ውስጥ ያሻውን እያደረገ ነው፡፡ በዘር ላይ ያተኮረ ቡድን ተሰማርቶ የሰራተኛውን ህልውና የሚነኩ ተግባራትን መፈፀም እስከ ማባረር ባለመብት መሆን፤ መቼም ልጆቻችሁ ይህን ጉዳይ በዚህ መልኩ ከያዙላችሁ እናንተ ደግሞ ብዙ ሚሊዮን ህዝብ በተራበበት ሀገር ባመቻቻችሁት የግብር ስርዐት ባጠራቀማችሁት ገንዘብ በትንሿ ልጃችሁ ስም ባደጉ ሀገራት ቤትና መኪና ገዝታችሁ ኑሮአችሁን እንዳመቻቻችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ለዛሬ እዚህ ላይ ብቃኝ፡፡ ወደፊት ደግሞ በኔ ላይ የደረሰውን ጨምሬ ከሌላ ጽሁፍ ጋር እንገናኛለን፡፡

በበ. ደ. ኮሬ፡ ቶሮንቶ፤ ካናዳ፤ ሰኔ፤ 2008/2016

No comments:

Post a Comment

wanted officials