Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, July 27, 2016

የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ አስቸኳይ ጥሪ እናደርጋለን:: ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ የተሰጠ መግለጫ





ከሕገመንግስታዊ አግባብ ዉጭ በዜጎች ላይ የሚወሰዱ የመንግስት እርምጃዎች እንዲቆሙ በፓርቲያችንም ሆነ የትግል ጓዶቻችን በሆኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ሲሰጡ የቆዩ ጋዜጣዊ መግለጫዎችንና ጋዜጣዊ ኮንፌረንሶች እናስታዉሳለን፡፡ በተለይም የዜጎቻችን ከፊንፊኔ ዙሪያ የማፈናቀል ድርጊት እንዲቆም ሲቀርቡ የቆዩ ተማፅኖዎች የመንግስት ባለሥልጣኖች ጆሮ እንዳልገባ አረጋግጠናል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለዉ ሥርአት ደጋፊዎች ጥቂት የማይባሉና ከአንድም በላይ ቤት ሲኖራቸዉ በመኖሪያ ቤት እጦት የሚቸገሩ ዜጎች ቁጥር የትየሌለ መሆኑና እነዚህም ዜጎች ከራሳቸዉና ከልጆቻቸዉ ጉሮሮ ቆጥበዉ የሰሩት መጠለያ፤ ለዚያዉም የክረምቱ ጊዜ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ ላይ ሲፈርስባቸዉ ማየት ምን ያህል ዘግናኝና አሳዛኝ እንደሆነ መድረክ ከሰጠዉ መግለጫ ለመረዳት ይቻላል፡፡


ምንም እንኳን መንግስት ሕግና ሕጋዊነትን የማስከበር ግዴታ ቢኖርበትም፤ ሰርቶ ለአገሪቱ ገቢ እያመጣ ጎጆዉን የሚቀልስ ብቻ ሳይሆን በእንፉቅቅ እየተንቀሳቀሰ ጎሮሮዉን ለሚዘጋ ዜጋ ሳይቀር መንግስት ኃላፊነት እንዳለበት ተዘንግቶ ዜጎች በድቅድቅ ጨለማ ክረምት ሜዳ ላይ መጣላቸዉ አሳዝኖናል፡፡

ቀደም ሲልም በልማትና እንቬስትመንት ስም በተለይም በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ስም ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የማያደርገዉንና በፊንፊኔ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሞ ሕዝብን ከቀዬያቸዉ የሚያፈናቅል ልማት ተብዬ እንቅስቃሴ እንዲቆም የኦሮሞ ሕዝብና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ከ2006 ጀምሮ በመቃወማችን በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስት በተወሰደዉ የኃይል እርምጃ 74 ዜጎች ተገድለዋል፡፡ በዚህ በ2008፤ በተለይም ከስምንት ወራት ወዲህ መንግስት ከሕዝብ ፍላጎት ዉጭ ጥቂቶች የሥርአቱ ደጋፊዎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገዉን፤ ነገር ግን መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ በተለይም የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የተቃወመዉን የሕዝብን ድምፅ እንደመስማት በማን አለብኝነት በወሰደዉ ያልተገባ እርምጃ እስካሁን ከ400 በላይ የኦሮሞ ዜጎች በመንግስት ኃይሎች ተገድለዋል፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፤ ከቀዬያቸዉና ከሥራቸዉ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ዜጎች ቁጥር ማወቅ አይቻልም፡፡

በመንግስት ኃይሎች በተወሰደዉ እርምጃ ነፍሰ ጡሮች፣ ዕድሜያቸዉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ለጋ ወጣቶች፣ ምሁራን፣ እናቶችና አዛዉንቶች ተገድለዋል፡፡ በቅርቡ እንኳን በምዕራብ ሸዋ ዞን በግንጪና በእጃጂ ወረዳዎች እንዲሁም በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በጉራዋና ሐረማያ ወረዳዎች ታዳጊ ወጣቶች የሆኑ ተማሪ እሸቱ ወርቁ ሞረዳ፣ ተማሪ ታረቀኝ ላቺሳ፣ ተማሪ ሣብሪና አብደላ እና ተማሪ ሪሐና አህመድ የተባሉት ራሳቸዉን በኦሮሞ ሕዝብ ጠላትነት በፈረጁ የመንግስት ኃይሎች ተገድለዋል፡፡ የእነዚህ ለጋ ወጣቶች ሕይወት መቀጠፍ የሚፈጥረዉን ስሜት ምን ሊመስል እንደሚችል የወላድ አንጀት ይፍረድ ከማለት ባለፈ ምንም ሊባልአይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ሆኑ የዓለም ሕብረተሰብ እንደሚመሰክረዉ የኦሮሞ ሕዝብ በበቀል ስሜት ተነሳስቶ በአንዳችም የሌላ ብሔር ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸም ቀርቶ ያሳየዉ የጥላቻ እርምጃ እስካሁን አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብን አርቆ አስተዋይነት ከማሳየቱም በላይ፤ ላቅ ባለ ደረጃ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከአፋኝ ሥርአት ጋር እንጂ ከጠባብ ፍላጎት ያልመነጨና ከንፁኃን ዜጎች ጋር አንዳች ቅራኔ እንደሌለዉ ያሳያል፡፡

ዛሬ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦፌኮ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የኢህአዴግን አገዛዝ የተቃወሙ የኦሮሞ ዘጎች በየእስር ቤቶች ታጉረዉ መገኘታቸዉ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከነዚህ ዉስጥም አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጉርሜሳ አያኖ፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ እነዮናታን ተስፋዬ፣ በረሃብ አድማ ላይ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ዜጎች ያለ ወንጀል የታሰሩ መሆኑ እየታወቀም ቢሆንም፤ ነገር ግን በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ቤተሰቦች፣ የትግል ጓዶችና ወገኖች ዉሳኔዉን እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ታሳሪዎቹ ወገኖቻችን በታሰሩበት ቦታ ላይ የሚደርስባቸዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ በመቃወም ለፍትሕ አካል ያቀረቡት አቤቱታ ሰሚ በማጣቱ በራሳቸዉ ላይ የወሰዱት ቀጣይ የተቃዉሞ እርምጃ እንጂ የቅንጦት አይደለም፡፡

እነዚህም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አቤቱታቸዉ እንዲሰማላቸዉ በራሳቸዉ ላይ በወሰዱት የምግብ አለመመገብ አድማ መሞት የለባቸዉም፡፡ የሕክምናና የነፍስ ማዳን ዕርዳታ ሊደርግላቸዉ ይገባል፡፡ እነዚህ ዜጎች በእንክብካቤ እጦት ቢሞቱ ዉሎ አድሮ የሚያስከትለዉ ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ የኢፌዲሪ መንግስት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሰብአዊ መብት ተከታታዮችና የዓለም ሕብረተሰብ በተለይም በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የሚትገኙ ዜጎች ይህንን የይድረሱልን ጥሪያችንን በመቀበል የእነዚህ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት ከሞት አፋፍ እንዲያተርፉልን የበኩላችሁን ድጋፍ እንዲታደርጉልን በእግዚአብሔርና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እንማፀናለን፡፡

በመብት ረገጣና እንግልት የሕዝቦች የመብትና የነፃነት ትግል አይገታም!

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ
ሐምሌ 20 ቀን 2008

No comments:

Post a Comment

wanted officials