በሰሜን ጎንደር የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ፍተሻው ተጠናክሯል
ሐምሌ ፲፫ ( አሥራ ሦስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በአማራ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በተለይም በሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ አውቶቡሶችና ሚኒባሶች በየቦታው እንዲቆሙ እየተደረገ ፣ ፖሊሶች መንገደኞችን እያስወረዱ መታወቂያ እየተቀበሉ ፍተሻ በማካሄድ ላይ ናቸው።
ተሳፋሪዎች በተደጋጋሚ እንዲፈተሹ በመደረጋቸው ምሬታቸውን እየገለጹ ነው። የጎንደሩ ህዝባዊ አመጽ ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች ይሸጋገራል የሚል ፍርሃት ማደሩ ለፍተሻው መጀመር ምክንያት መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።
በሌላ በኩል በኦሮምያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደው ተቃውሞ በጎንደር ከታዬው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በመላ አገሪቱ በማንኛውም ጊዜ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የኢሳት ወኪሎች ከተለያዩ አካባቢዎች ያሰባሰቡት መረጃ ያመለክታል። በአዲስ አበባ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ በየጊዜው እየተጠሩ ኢህአዴግን እንዲቀላቀሉ ፣ አባል ካልሆኑ ግን ችግር እንደሚገጥማቸው ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ነው። ወላጆች እየተጠሩ ልጆቻቸውን እንዲቆጣጠሩም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በሚደረጉ ስብሰባዎች ዜጎች አርበኞች ግንቦት7፣ የኤርትራን መንግስት፣ ኢሳትንና የአሜሪካ ድምጽን እንዲያወግዙ እየተጠየቁ መሆኑን ወኪላችን ገልጿል።
No comments:
Post a Comment