በባህርዳር የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጎንደር በህዝቡ ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተቃወሙ
ሐምሌ ፲፱ ( አሥራ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የትግራይ ክልል የደህንነትና የፖሊስ አባላት የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላትን ለመያዝ ወደ ጎንደር በተንቀሳቀሱበት ወቅት የኮሚቴው አባል የሆኑት ኮ/ል ደመቀ ዘውዴን “ ህገወጥ በሆነ መንገድ አልያዝም” በማለት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ፣ በሰሜን ጎንደር ህዝብና በመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ 19 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ 18ት ደግሞ መቁሰላቸው ባለፈው ሃሙስ በባህርዳር በሰፈረው የሰሜን ምእራብ እዝ የመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ወይም በተለምዶ አጠራር መኮድ በተደረገው ዝግ ስብሰባ ይፋ ሆኗል። ይህን ተከትሎ በተደረገው የሰራዊት ግምገማ ስብሰባውን የሚመሩት የሰሜን ምእራብ እዝ አዛዥ ሌ/ጄ ብርሃኑ ጁላ ፣ “ ይህ ሁሉ ሰራዊት ሲጨፈጨፍ ምን ትሰሩ ነበር?” የሚል ጥያቄ በቁጣ ሲያነሱ፣ የሰራዊቱ አባላት ዝምታን በመመርጥ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበሩንም።
አዛዡ “ወታደሮቹ ሲደበደቡ ጋንታ መሪዎች ምን እርምጃ ይወስዱ ነበር?እነሱ ሲደበደቡ ዝም ብለው ያዩት ከጀርባቸው አንድ ነገር እንዳለ ያሳያልና እርምጃ ይወሰድባቸዋል” በማለት በጋንታ አመራሮች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ወታደሮች አስተያየት ላለመስጠት በሚመስል መልኩ ለደቂቃዎች ዝምታን የመረጡ ቢሆንም፣ አንድ የአካባቢው ተወላጅ ወታደር ግን እጁን በማውጣት “ የሰራዊቱ ተግባር ድንበር ማስጠበቅ ነው ወይስ በወገኑ ላይ አላስፈላጊ እርምጃ መውሰድ? ጅምላ ግደሉ ከተባልን መመሪያ ይሰጠንንና በህዝቡ ላይ እርምጃ እንወስዳለን፣ መመሪያውን እስካላወቅን ድረስ ምንም ማድረግ አንችልም” የሚል አስተያየት ሲያቀርብ፣ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት አስተያየቱን በመደገፍ እጃቸውን ያወጡ ሲሆን፣ የስብሰባው መሪ የቤቱን አስተያየት በማዬት በብስጭት “ እያንዳንድህ ለራስህ ህልውና ስትል እርምጃ የማትወስድ ከሆነ ድብን ያድርግህ፣ እኛ ለአንተ እርምጃ አንወስድም” የሚል ሃይለቃል በመናገር ስብሰባው የታለመለትን ግብ ሳያሳካ እንዲበተን ተደርጓል።
የሰራዊቱ አባላት ውጭ ከወጡ በሁዋላ “ መንግስት ስርዓቱን ማስቀጠል ሲያቅተውና አገር መምራት አለመቻሉ ሲሰማው፣ እኛ በህዝባችን ላይ እርምጃ እንድንወስድ የሚያግባባን እኛ ፖለቲካ አናውቅም ወይ?” በማለት ሲናገገሩ እንደነበር የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የሰሜን ምእራብ እዝ ወታደሮች በህዝብ ላይ ለመተኮስ ፈቀደኛ አለመሆናቸው ፣ ገዢው ፓርቲ ችግሩን በድርድር እንፍታው ብሎ እንዲማጸን ሳያደርገው አልቀረም። በአካባቢው የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ ለማብረድ ገዢው ፓርቲ ከሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ይልቅ አጋዚ ኮማንዶዎችን መጠቀም መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሃምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም የሰሜን ጎንደር ህዝብ የታሰሩ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ምንነት የኮሚቴ አባላት እንዲሁም በማረሚያ ቤት የሚገኙት ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ እንዲለቀቁ በሰላማዊ ሰልፍ ይጠይቃል። ሰልፉ እንዳይካሄድ የተለያዩ ጫናዎች እና የማዘናጊያ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ቢሆንም፣ በህዝቡ በኩል የሚታዬው ህዝባዊ ቁጣ ገዢው ፓርቲ ለውሳኔ እንዲቸገር እድርጎታል።
No comments:
Post a Comment